ሳኦል በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ እስራኤልንም አርባ ሁለት ዓመት ገዛ። ሳኦል ከእስራኤል ሦስት ሺሕ ሰዎች መረጠ። ሁለቱ ሺሕ በማክማስና በኰረብታማው አገር በቤቴል ከሳኦል ጋራ፣ አንዱ ሺሕ ደግሞ በብንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋራ ነበሩ። የቀሩትን ሰዎች ግን ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አሰናበተ። ዮናታን ጌባዕ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም፣ “ዕብራውያን ይስሙ!” በማለት በምድሪቱ ሁሉ መለከት አስነፋ። ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ርኩስ ተቈጥራ ተጠላች” የሚለውን ወሬ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ። ፍልስጥኤማውያን ሦስት ሺሕ ሠረገሎች፣ ስድስት ሺሕ ፈረሰኞች ቍጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሰራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በስተምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ። እስራኤላውያን፣ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሠጋ መሆኑንና ሰራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፣ በየዋሻውና በየእሾኽ ቍጥቋጦው፣ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጕድጓዱ ሁሉ ተደበቁ። ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን በጌልገላ ቈየ፣ ዐብሮት የነበረውም ሰራዊት ሁሉ በፍርሀት ይንቀጠቀጥ ነበር። እርሱም ሳሙኤል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰራዊት መበታተን ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። ልክ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ፣ ወዲያውኑ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊቀበለው ወጣ። ሳሙኤልም፣ “ያደረግኸው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሰራዊቱ መበታተኑን፣ አንተም በቀጠርኸው ጊዜ አለመምጣትህን፣ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን አየሁ፤ ‘ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ወርደው ወደ ጌልገላ ይመጡብኛል፤ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም’ ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ።” ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ጠብቀኸው ቢሆን ኖሮ፣ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቷል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመጠበቅህም፣ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።” ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳኦልም ዐብረውት የነበሩትን ሰዎች ቈጠራቸው፤ ብዛታቸውም ስድስት መቶ ያህል ነበረ።
1 ሳሙኤል 13 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 13:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች