መጽ​ሐፈ ነገ​ሥት ቀዳ​ማዊ 16:1-28

መጽ​ሐፈ ነገ​ሥት ቀዳ​ማዊ 16:1-28 አማ2000

የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቃል ስለ ባኦስ እን​ዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ። “እኔ ከመ​ሬት አን​ሥቼ በሕ​ዝቤ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ አለቃ አድ​ር​ጌ​ሃ​ለሁ፤ አንተ ግን በከ​ንቱ ጣዖ​ታ​ቸው ያስ​ቈ​ጡኝ ዘንድ ሕዝ​ቤን እስ​ራ​ኤ​ልን በአ​ሳ​ታ​ቸው በኢ​ዮ​ር​ብ​ዓም መን​ገድ ሄድህ፤ ስለ​ዚ​ህም፥ እነሆ፥ ባኦ​ስ​ንና ቤቱን ፈጽሜ አጠ​ፋ​ለሁ፤ ቤት​ህ​ንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮ​ር​ብ​ዓም ቤት አደ​ር​ጋ​ለሁ። ከባ​ኦ​ስም ወገን በከ​ተ​ማ​ዪቱ ውስጥ የሚ​ሞ​ተ​ውን ውሾች ይበ​ሉ​ታል፤ በሜ​ዳ​ውም የሚ​ሞ​ተ​ውን የሰ​ማይ ወፎች ይበ​ሉ​ታል።” የቀ​ረ​ውም የባ​ኦስ ነገር፥ የሠ​ራ​ውም ሁሉ፥ ኀይ​ሉም ሁሉ፥ በእ​ስ​ራ​ኤል ነገ​ሥ​ታት የታ​ሪክ መጽ​ሐፍ የተ​ጻፈ ነው። ባኦ​ስም ከአ​ባ​ቶቹ ጋር አን​ቀ​ላፋ፥ በቴ​ር​ሳም ተቀ​በረ፤ ልጁም ኤላ በአሳ በሃያ ስድ​ስ​ተ​ኛው ዓመተ መን​ግ​ሥት በፋ​ን​ታው ነገሠ። በእ​ጁም ሥራ ያስ​ቈ​ጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮ​ር​ብ​ዓም ቤት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ስላ​ደ​ረ​ገው ክፋት ሁሉ እር​ሱ​ንም ስለ ገደ​ለው፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል በባ​ኦ​ስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢዩ መጣ። የባ​ኦ​ስም ልጅ ኤላ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ በቴ​ርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ። የእ​ኩ​ሌ​ቶቹ ፈረ​ሶች አለቃ ዘም​ሪም አሽ​ከ​ሮ​ቹን ሁሉ ሰብ​ስቦ ዐመፀ፤ ኤላም በቴ​ርሳ ነበረ፤ በቴ​ር​ሳም በነ​በ​ረው በመ​ጋ​ቢው በአሳ ቤት ይሰ​ክር ነበር። በይ​ሁ​ዳም ንጉሥ በአሳ በሃያ ሰባ​ተ​ኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ ወጋና ገደ​ለው፤ በፋ​ን​ታ​ውም ነገሠ። ከነ​ገ​ሠና በዙ​ፋ​ኑም ከተ​ቀ​መጠ በኋላ፥ የባ​ኦ​ስን ቤት ሁሉ አጠፋ፤ አንድ ወንድ እንኳ አላ​ስ​ቀ​ረ​ለ​ትም። በነ​ቢዩ በኢዩ አፍ በባ​ኦስ ቤት ላይ እንደ ተና​ገ​ረው እንደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል፥ ባኦ​ስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኀጢ​አት ሁሉ፥ በር​ኵ​ሰ​ታ​ቸው የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ያስ​ቈ​ጡት ዘንድ እስ​ራ​ኤ​ልን ስለ አሳ​ቱ​በት ኀጢ​አት፥ ዘምሪ የባ​ኦ​ስን ቤት ሁሉ እን​ዲሁ አጠፋ። የቀ​ረ​ውም የኤላ ነገር፥ ያደ​ረ​ገ​ውም ሁሉ፥ በእ​ስ​ራ​ኤል ነገ​ሥ​ታት የታ​ሪክ መጽ​ሐፍ የተ​ጻፈ ነው። በይ​ሁ​ዳም ንጉሥ በአሳ በሃያ ዘጠ​ነ​ኛው ዓመት ዘምሪ በቴ​ርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። የእ​ስ​ራ​ኤል ሠራ​ዊት ግን በፍ​ል​ስ​ጥ​ኤም ሀገር በገ​ባ​ቶን ሰፍ​ረው ነበር። በሰ​ፈር ያሉ ሕዝ​ቡም “ዘምሪ ከድቶ ኤላን ገደ​ለው፥ በፋ​ን​ታ​ውም ነገሠ” ሲሉ ሰሙ። እስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰ​ፈሩ ውስጥ የሠ​ራ​ዊ​ቱን አለቃ ዘን​በ​ሪን አነ​ገሡ። ዘን​በ​ሪም ከእ​ርሱም ጋር እስ​ራ​ኤል ሁሉ ከገ​ባ​ቶን ወጥ​ተው ቴር​ሳን ከበቡ። በእ​ር​ስ​ዋም ተቀ​መጡ። ዘም​ሪም ከተ​ማ​ዪቱ እንደ ተያ​ዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፤ የን​ጉ​ሡ​ንም ቤት በራሱ ላይ በእ​ሳት አቃ​ጠለ፤ ሞተም። ስላ​ደ​ረ​ገ​ውም ኀጢ​አት፥ እስ​ራ​ኤ​ል​ንም ስላ​ሳ​ተ​በት ኀጢ​አት፥ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ክፉ አድ​ር​ጎ​አ​ልና፥ በና​ባጥ ልጅ በኢ​ዮ​ር​ብ​ዓ​ምም መን​ገድ ሄዶ​አ​ልና ሞተ። የቀ​ረ​ውም የዘ​ምሪ ነገር፥ ያደ​ረ​ገ​ውም ዐመፅ፥ በእ​ስ​ራ​ኤል ነገ​ሥ​ታት የታ​ሪክ መጽ​ሐፍ የተ​ጻፈ ነው። በዚ​ያም ጊዜ የእ​ስ​ራ​ኤል ሕዝብ በሁ​ለት ተከ​ፈለ፤ የሕ​ዝ​ቡም እኩ​ሌታ የጎ​ና​ትን ልጅ ታም​ኒን ያነ​ግ​ሡት ዘንድ ተከ​ተ​ሉት፤ እኩ​ሌ​ቶ​ችም ዘን​በ​ሪን ተከ​ተሉ። ዘን​በ​ሪ​ንም የተ​ከ​ተሉ ሕዝብ የጎ​ናት ልጅ ታምኒን የተ​ከ​ተ​ሉ​ትን ሕዝብ ድል አደ​ረ​ጉ​አ​ቸው፤ ታም​ኒም ሞተ፤ ወን​ድ​ሙም ኢዮ​ራም በዚ​ያው ዘመን ሞተ፤ ከታ​ምኒ በኋላ ዘን​በሪ ነገሠ። በይ​ሁዳ ንጉሥ በአሳ በሠ​ላሳ አን​ደ​ኛው ዓመተ መን​ግ​ሥት ዘን​በሪ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ ዐሥራ ሁለት ዓመት ነገሠ። በቴ​ር​ሳም ስድ​ስት ዓመት ነገሠ። ዘን​በ​ሪም ከዚ​ያች ተራራ ባለ​ቤት ከሴ​ሜር በሁ​ለት መክ​ሊት ብር የሳ​ም​ሮ​ንን ተራራ ገዛ፤ በተ​ራ​ራ​ውም ላይ ከተማ ሠራ፤ የሠ​ራ​ት​ንም ከተማ በተ​ራ​ራው ባለ​ቤት በሳ​ምር ስም ሰማ​ርያ ብሎ ጠራት። ዘን​በ​ሪም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ክፉ አደ​ረገ፤ ከእ​ር​ሱም አስ​ቀ​ድሞ ከነ​በ​ሩት ይልቅ እጅግ ከፋ። በና​ባ​ጥም ልጅ በኢ​ዮ​ር​ብ​ዓም መን​ገድ ሁሉ በር​ኩ​ስ​ነ​ታ​ቸው የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ያስ​ቈ​ጡት ዘንድ እስ​ራ​ኤ​ልን ባሳ​ተ​በት ኀጢ​አት ሄደ። የቀ​ረ​ውም ዘን​በሪ ያደ​ረ​ገው ነገር፥ የሠ​ራ​ውም ጭከና፥ በእ​ስ​ራ​ኤል ነገ​ሥ​ታት የታ​ሪክ መጽ​ሐፍ የተ​ጻፈ ነው። ዘን​በ​ሪም ከአ​ባ​ቶቹ ጋር አን​ቀ​ላፋ፥ በሰ​ማ​ር​ያም ቀበ​ሩት፤ ልጁም አክ​አብ በፋ​ን​ታው ነገሠ። 28 ‘ሀ’ ዘን​በ​ሪም ዐሥራ አንድ ዓመት ሲሆ​ነው የአሳ ልጅ ኢዮ​ሳ​ፍጥ ነገሠ። በነ​ገ​ሠም ጊዜ ሠላሳ አም​ስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ሃያ አም​ስት ዓመት ነገሠ፤ እና​ቱም ጋዙባ የም​ት​ባል የሴ​ላህ ልጅ ነበ​ረች። 28 ‘ለ’ በአ​ባ​ቱም በአሳ መን​ገድ ሄደ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ጽድ​ቅን ያደ​ርግ ዘንድ ከእ​ር​ስዋ ፈቀቅ አላ​ለም። በተ​ራ​ሮች የነ​በ​ሩ​ት​ንም አማ​ል​ክት አላ​ስ​ወ​ገ​ደም፤ ሕዝ​ቡም በተ​ራ​ሮቹ ይሠ​ዉ​ላ​ቸ​ውና ያጥ​ኑ​ላ​ቸው ነበረ። 28 ‘ሐ’ ኢዮ​ሳ​ፍ​ጥም ከእ​ስ​ራ​ኤል ንጉሥ ጋር የሠ​ራው፥ የተ​ዋ​ጋ​ውና ያደ​ረ​ገው ኀይል ሁሉ እነሆ፥ በይ​ሁዳ ነገ​ሥ​ታት የታ​ሪክ መጽ​ሐፍ የተ​ጻፈ ነው። 28 ‘መ’ በአ​ባ​ቱም በአሳ ዘመን የነ​በ​ረ​ውን ርኵ​ሰት ሁሉ ከም​ድር አስ​ወ​ገደ። በኤ​ዶ​ምም ንጉሥ አል​ነ​በ​ረም። 28 ‘ሠ’ ንጉሥ ኢዮ​ሳ​ፍ​ጥም ወር​ቅና ብርን ሊያ​መ​ጡ​ለት ወደ አፌር ይልክ ዘንድ በተ​ር​ሴስ መር​ከብ አሠራ፤ በጋ​ስ​ዮንጋቤር የነ​በ​ረ​ችው መር​ከብ ተሰ​ብ​ራ​ለ​ችና አል​ሄ​ደ​ችም። 28 ‘ረ’ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ንጉሥ አካ​ዝ​ያስ ኢዮ​ሳ​ፍ​ጥን፥ “አገ​ል​ጋ​ዮ​ች​ህ​ንና አገ​ል​ጋ​ዮቼን በመ​ር​ከብ እን​ላክ” አለው። ኢዮ​ሳ​ፍ​ጥም እንቢ አለ። 28 ‘ሰ’ ኢዮ​ሳ​ፍ​ጥም እንደ አባ​ቶቹ አን​ቀ​ላፋ። በዳ​ዊ​ትም ከተማ ከአ​ባ​ቶቹ ጋር ተቀ​በረ። በእ​ር​ሱም ፋንታ ልጁ ኢዮ​ራም ነገሠ።