1 ነገሥት 16:1-28

1 ነገሥት 16:1-28 NASV

ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ሲል ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ፤ “ከትቢያ አንሥቼ፣ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ ሕዝቤ እስራኤል ኀጢአት እንዲሠራ፣ በኀጢአቱም ለቍጣ እንዲያነሣሣኝ አሳሳትኸው። ስለዚህ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርገዋለሁ። በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞቱትን የባኦስን ወገኖች ሁሉ ውሾች ይበሏቸዋል፤ በገጠር የሚሞቱትንም ሁሉ የሰማይ አሞሮች ይቀራመቷቸዋል።” በባኦስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ ሌላው ያደረገው ሥራው በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? ባኦስ፣ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በቴርሳም ተቀበረ። ልጁም ኤላ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። ከዚህም በቀር የእግዚአብሔር ቃል በአናኒ ልጅ፣ በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባኦስና በቤቱ ላይ የመጣበት ምክንያት፣ በእጁ ሥራ ያስቈጣው ዘንድ እንደ ኢዮርብዓም ቤት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራን ሁሉ በማድረጉና ኢዮርብዓምን በማጥፋቱም ጭምር ነው። የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በቴርሳ ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ። ከሹማምቱ አንዱና የግማሽ ሠረገሎቹ አዛዥ የሆነው ዘምሪ ዐምፆ ተነሣበት፤ በዚያ ጊዜ ኤላ በቴርሳ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው በአርጻ ቤት ጠጥቶ ሰክሮ ነበር፤ ዘምሪም ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነገሠ። ዘምሪ ወዲያው እንደ ነገሠና በዙፋን እንደ ተቀመጠ፣ የባኦስን ቤተ ሰብ በሙሉ ገደለ፤ የሥጋ ዘመድም ሆነ ወዳጅ አንድም ወንድ አላስቀረም። በዚህ ሁኔታም በነቢዩ በኢዩ አማካይነት በባኦስ ላይ በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የባኦስን ቤተ ሰብ ሁሉ ፈጀ። ይህም የሆነው ባኦስና ልጁ ኤላ፣ በማይረቡ ጣዖቶቻቸው ምክንያት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ በሠሩት ኀጢአት ሁሉና፣ እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ነበር። ሌላው ኤላ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሆኖ ሰባት ቀን ብቻ ገዛ። በዚህ ጊዜ ሰራዊቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ የሆነችውን ገባቶንን ከብቦ ሰፍሮ ነበር። በዚያም ሰፈር የነበሩ እስራኤላውያን ዘምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን እንደ ሰሙ፣ የሰራዊቱን አዛዥ ዖምሪን በዚያ ዕለት እዚያው ሰፈር ውስጥ በእስራኤል ላይ ማንገሣቸውን ዐወጁ። ከዚያም ዖምሪና ዐብረውት ያሉት እስራኤላውያን ሁሉ ከገባቶን ወደ ላይ ወጥተው ቴርሳን ከበቡ። ዘምሪ ከተማዪቱ መያዟን ሲያይ፣ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወዳለው ግንብ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበትና በዚሁ ሞተ። ይህ የሆነውም በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ በመሥራትና በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድ፣ እንዲሁም ራሱ በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ ባደረገው ኀጢአት ምክንያት ነው። ሌላው ዘምሪ በዘመኑ የፈጸመው ድርጊትና ያካሄደውም ዐመፅ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ ከሁለት ተከፈለ፣ ይህም ግማሹ የጎናትን ልጅ ታምኒን ለማንገሥ ሲሆን፣ የቀረው ደግሞ ዖምሪን በመደገፍ ነበር። ሆኖም የዖምሪ ተከታዮች ከጎናት ልጅ ከታምኒ ተከታዮች ይልቅ በረቱ፤ ስለዚህ ታምኒ ሞተ፤ ዖምሪም ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሠላሳ አንደኛው ዓመት፣ ዖምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ሁለት ዓመትም ገዛ፤ ከዚህም ውስጥ ስድስቱን ዓመት የገዛው በቴርሳ ሆኖ ነው። እርሱም የሰማርያን ኰረብታ በሁለት መክሊት ጥሬ ብር ከሳምር ላይ ገዝቶ ከተማ ሠራባት፤ ስሟንም በቀድሞው የተራራዋ ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራት። ይሁን እንጂ ዖምሪ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ ከርሱ አስቀድሞ ከነበሩትም ይልቅ የበለጠ ኀጢአት ሠራ። እርሱም እስራኤል በማይረቡ ጣዖቶቻቸው፣ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ እንዲያነሣሡት ባደረገው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሁሉና እርሱም ኀጢአት ሠርቶ እስራኤልም እንዲሠሩ ባደረገው ኀጢአት ተመላለሰ። ሌላው ዖምሪ በዘመኑ የፈጸመው፣ ያደረገውና ያከናወነው ሁሉ በእስራኤል የነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? ዖምሪ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ ልጁም አክዓብ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።