መጽሐፈ ጥበብ 9

9
ጥበብን ለማግኘት ሰሎሞን ያቀረበው ጸሎት
1የአባቶቻችን አምላክ፥ የምሕረት ጌታ፥#መዝ. 86፥15።
መላውን ዓለም በቃልህ ፈጠርክ፤#ዘፍ. 1፤ መዝ. 33፥6፤ ምሳ. 3፥19፤ ኤር. 10፥12፤ ዮሐ. 1፥3፤10።
2ፍጡራንህንም ይገዛ ዘንድ፥
የሰውን ልጅ በጥበብህ ሠራህ፤#መዝ. 8፥7፤ ሲራ. 17፥2።
3ዓለምን በቅድስና ለመግዛት፥ ፍትሕንም ለመጠበቅ፥
በነፍስ ታማኝነት ያልተዛባ ፍርድ ለመስጠት፥#1ነገ. 3፥6፤ 9፥4፤ መዝ. 9፥8።
4በዙፋንህ የምትቀመጥ ጥበብን ስጠኝ፤
ከልጆችህም መሀል አትነጥለኝ።#2ዜ.መ. 1፥10።
5እኔ አገልጋይህ የአገልጋይትህ ልጅ፥
ለአጭር ጊዜ የምኖር ደካማ ሰው፥
ስለ ሕጎችህና ስለ ፍትሕ የማላውቅ ነኝና።#1ነገ. 3፥7፤ መዝ. 116፥16።
6አንድ ፍጹም ከሰዎች መካከል ቢኖር እንኳን፥
ያንተ የሆነችውን ጥበብ ካላገኘ ቁጥሩ ከከንቱዎች ነው።#ጥበ. 3፥17፤ 1ነገ. 11፥4፤ 1ቆሮ. 3፥18።
7በሕዝቦችህ ላይ እንድነግሥ መረጥኸኝ፤
በወንድና በሴት ልጆችህም ላይ እንድፈርድ ፈቀድክ።#1ዜ.መ. 28፥5።
8በቅዱሱ ተራራ ላይ ቤተ መቅደስህን እንድገነባ፥
ድንኳንህን በተከልክበት ከተማ፥ ጥንት ያዘጋጀሃትን የቀደሰች ድንኳን ዓይነት፥
መሠዊያህን እንድሠራ አዘዝከኝ።#ዘፀ. 25፥8፤ 2ሳሙ. 7፥13፤ 1ዜ.መ. 28፥5፤ 2ዜ.መ. 6፥1፤ 7፥7፤ ጦቢ. 1፥4፤ መዝ. 15፥1፤ 48፥2።
9ዓለምን በፈጠርህ ጊዜ ከጐንህ ያልተለየችው፥
ሥራዎችህን የምታውቀው ጥበብ ካንተ ጋር ናት።
አንተን ደስ የሚያሰኘውን፥
ከትእዛዞችህ ጋር የሚስማማውን ሁሉ ታውቃለች።#ዘዳ. 6፥7፤ ምሳ. 8፥22-31፤ ዮሐ. 1፥1፤ 10።
10እኔን እንድትረዳኝ፥ ከእኔ ጋር እንድትደክም፥
አንተን የሚያስደስትህን እንድታስምረኝ፥
ከቅዱሳን ሰማያት አውጣት፤
ከከበረው ዙፋንህም ወደዚህ ላካት።#ጥበ. 18፥15፤ ማቴ. 5፥34፤ ዮሐ. 3፥17፤ 20፤ 21።
11ሁሉንም የምታውቅና የምትረዳ በመሆኗ፥
በሥራዎቼ ላይ ሁሉ በጥንቃቄ ትመራኛለች፤
ክብሯም ትጠብቀኛለች።#ጥበ. 8፥8።
12ያኔ የማደርገው ሁሉ ተቀባይነትን ያገኛል፤
ሕዝብህን በትክክል እመራለሁ፤
ለአባቴ ዙፋንም የተገባሁ እሆናለሁ።#1ነገ. 3፥6-9።
13የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊያውቅ የሚችል ሰው ማን ነው?
የጌታንስ ፈቃድ በውል የሚገነዘብ ማን ነው?#ኢሳ. 40፥13፤ ባሮክ 3፥31።
14የሰዎች ግንዛቤ በስህተት የተሞላ ነው፤
አመለካከታቸውም ወላዋይ ነው፤
15ፈራሹ ሥጋ ነፍስን ይከብዳታል፥
ምድራዊው ድንኳንም የሚያስብ ልቡናን ይጫነዋል።#ኢዮብ 4፥19።
16በምድር ላይ ያለውን ለማወቅ እንቸገራለን፤
ባጠገባችን ያለውንም ለመረዳት እንደክማለን፤
እንግዲያውስ በሰማያት ያለውን ሊያውቅ የሚችል ከቶ ማን ነው?#ሲራ. 1፥3፤ ዮሐ. 3፥12።
17አንተ ጥበብን ባትሰጥ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ባትልክ ኖሮ፥
ማን ፈቅድህን ሊያውቅ ይችል ነበር?#ዮሐ. 14፥26።
18በዚህ ዓይነት የምድር ነዋሪዎች መንገድ ተቃና፤
ሕዝቦች ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ ተማሩ፤
በጥበብም ዳኑ።#ጥበ. 10፥9፤ ምሳ. 28፥26።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ