መጽሐፈ ጥበብ 5

5
1ጻድቁ ግን በድፍረት ይቆማል፤
ጨቋኞቹን ግንባሩን ሳያጥፍ ይመለከታል፥
ስላሳለፈው መከራም አያስብም።
2እርሱን ባዩ ጊዜ ኃጥአን በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ፤
ባልተጠበቀ ሁኔታም በመዳኑ ይደነቃሉ።
3በጸጸት እየተቃጠሉ፥ ሢቃ እየተናነቃቸው፥
ትንፋሻቸው ቁርጥ ቁርጥ እያለ እንዲህ ይባባላሉ፥
4ስንሳለቅበት የነበረው እርሱ ነው፤ እናላግጥበትም ነበር፤
ምንኛ ተሞኝተናል፤ ሕይወቱን እንደ እብደት፥
አሟሟቱንም ወራዳ አድረገን ቆጥረን ነበር።
5እንደምን ከእግዚአብሔር ልጆች እንደ አንዱ ሊቆጠር ቻለ?
ዕጣውስ ከቅዱሳን ጋር እንደምን ተመሳሰለ?
6በእርግጥም ከእውነት መንገድ ወጥተናል፤
የፍትሕ ብርሃን ለእኛ አላበራልንም፤
ፀሐይም አልወጣችልንም።
7እኛ ያልተጓዝንበት የጥፋትና የክፋት መንገድ የለም፤
መንገድ በሌለበት በረሃ አቋርጠናል፤
የእግዚአብሔርን መንገድ ግን አናውቀውም ነበር።
8ግትርነት ምን ጠቀመን?
ሀብትስ ሆነ ትዕቢት ምን በጀን?
9እኒያ ሁሉ ክፉ ሥራዎች እንደ ጥላ፥
እንደ በራሪ ወሬም አለፉ።
10የክፉ ሞገድን ሰንጥቆ ሲያልፍ፥
ያለፈበትን መንገድ ዱካ እንደማይተውና
ደጋፊ ብረቱም ላይ አሻራውን እንደማያሳርፍ መርከብ ነው።
11ወይም በአየር ላይ እንደምትበር፥
ስለ ማለፍዋ ግን ማስረጃ እንደማትተው ወፍም ሊሆን ይችላል፤
ወፍዋ አየሩን በክንፎቿ ትቀዝፋለች፥
ከኋላዋ ግን ስለ ማለፍዋ ምልክት የለም።
12ወይም በአንድ ኢላማ ላይ የወረወረ ፍላጻ በስቶት ያለፈው አየር መልሶ እንደሚገጥም፥
ፍላጻውም በየትኛው አቅጣጫ እንደተወረወረ ለማወቅ እንደማይቻለው ዓይነት ነው።
13እኛም እንዲሁ ነን፤ ከመወለዳችን እንጠፋለን፤ መልካም ሥነ ምግባር የለንም፤
በክፉ ሥራችን ተውጠን ጠፍተናል።
14የክፉ ሰው ተስፋ ነፍስ እንደወሰደው ገለባ፥
ማዕበል እንደገፋው ረቂቅ ውሃ፥
ነፋስ እንደበተነው ጢስ፥
እንደ አንድ ቀን እንግዳ ትዝታ ወዲያው ይጠፋል።
አስደሳቹ የጻድቃን ፍጻሜና የኃጥአን ቅጣት
15ጻድቃን ግን ለዘለዓለም ይኖራሉ፤
ካሣቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤
እርሱ ይጠብቃቸዋል፤
16ታላቁን ዘውድ ይደፋሉ፤
ከጌታ እጅ የውበትን አክሊል ይቀበላሉ፤
በቀኝ እጁ ይጠብቃቸዋል፤ በክንዱም ይከልላቸዋልና።
17ቀናተኛ ፍቅሩ ትጥቅ ነው፤
ጠላቶቹን ለመቅጣት ፍጡራንን ሁሉ ያስታጥቃል።
18ፍትሕና ጥሩር፥ የማያዳግመውን ቀናተኛ ፍርዱን፥ የራስ ቁር ያደርገዋል፤
19የማይታጠፈውን ቅድስና ጋሻ፥
የማይበርድ ቁጣውን ሠይፍ ያደርጋል፤
ዓለምም ግድየለሾችን ለመውጋት አብራው ትዘምታለች።
20በሚገባ የታለሙት ጨረሮች፥ እኒያ መብረቃዊ ጦሮች ይወነጨፋሉ፤
21በደምብ ከተወጠረ ቀስት፥ እንደሚምዘገዘግ ፍላጻም፥
ከደመናዎች ውስጥ ኢላማቸውን ለመምታት ይፈተለካሉ።
22ወስፈንጠሩ በቁጣ የተሞሉ በረዶዎችን ያዘንባል፤
የባሕር ውሃዎች በእነርሱ ላይ ይነሳሉ፤
ወንዞችም ያለ ምሕረት ያጥለቀልቋቸዋል።
23ኃይለኛ ነፋስ በእነርሱ ላይ ይነፍሳል፤
እንደ ዓውሎ ነፋስም ያበጥራቸዋል።
ኃጢአት ምድርን ወና ያስቀራታል፤
ክፋትም የኃያላኑ ዙፋን ያነኳኩተዋል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ