መጽሐፈ ጥበብ 12

12
1ሕያው የሆነው መንፈስህ በሁሉም ነገር ውስጥ ወርዷል!
2ቀስ በቀስም አጥፊዎችን ታርማለህ፥
ኃጢአታቸውን ታስታውሳቸዋለህ፥ ትገስጻቸዋለህም፤
ጌታ ሆይ ይህንንም ያደረግኸው
ከክፋት እንዲርቁና ባንተም ያምኑ ዘንድ ነው።
እግዚአብሔር በከነዓናውያን ላይ ያሳየው ትዕግስት
3 # ዘዳ. 12፥31፤ 18፥9-13። በቅድስት መሬትህ ላይ
የነበሩትን የቀደሙ ሰፋሪዎች
4በሥራዎቻቸው አስጸያፊነት ጠላሃቸው፤
ያልተቀደሱ ስርዓቶቻቸውንና አስማቶቻቸውን አልወደድህም።
5ሕፃናትን የሚገድሉ ምሕረት የለሾች፥
በበዓላት ላይ የሰውን ስጋና ደም፥
የሆድ ዕቃውንም የሚበሉ ሰው በላዎች፥
የምሥጢራዊ ወንድማማችነት ምልምሎች፥
6እኒያ ራሳቸውን ማዳን የማይችሉ ሕፃናትን የሚገድሉ ወላጆች፥
በአባቶቻችን እጅ ይጠፉ ዘንድ ፈረድህ፤
7ከሁሉም በላይ የምትወዳት ይህች መሬትም
የእግዚአብሔርን ልጆች ታስተናግድ ዘንድ ፈቀድህ።
8 # ዘፀ. 23፥28። እነኚህንም እንኳ ሰዎች በመሆናቸው ራራኽላቸው፤
ከሠራዊትህ ፊት ፊት ተርቦችን በመላክ
ጥቂት በጥቂት አጠፋሃቸው።
9በተፋፋመ ጦርነት መሀል ክፉዎችን በጻድቃኖች እጅ መጣል ችግርህ አልነበረም፤
ወይንም እነርሱን በአስፈሪ አውሬዎች አልያም በቁጣ ቃል ልታጠፋቸውም በቻልህ ነበር፤
10ምንም እንኳ እነርሱ በክፋት የተጠነሰሱ መሆናቸውን ብታውቅም፥
በተፈጥሮአቸው ክፉዎች ቢሆኑም፥
11ከመጀመሪያው የተረገሙ ዘሮች መሆናቸው
ሐሳባቸውን እንደማይሽሩ ብትገነዘብም፥
ፍርድህን ቀስ በቀስ በማሳየት
ይጸጸቱ ዘንድ እድል ሰጥተሃቸዋል፤
ስለ ኃጢአታቸው ያልቀጣሃቸው ማንንም ፈርተህ አልነበረም።
የእግዚአብሔር ቻይነት ሲብራራ
12ያደረግኸው ምንድነው?
በማለት ሊጠይቅህ የሚደፍር፥
ፍርድህንም የሚቃወም የለምና።
የፈጠርኻቸውን ሕዝቦች ብትደመስስ ከሳሽህ ከቶ ማነው?
ክፉዎችን በመደገፍ አንተን የማጋፈጥ ይኖራልን?
13ካንተ በላይ ስለ ሁሉም የሚጨነቅ፥
ፍርድህም ትክክለኛ እንደሆነ የምታረጋግጥለት፥
ሌላ አምላክ የለም።
14ንጉሥም ቢሆን ፈላጭ ቆራጭ፤
ብይንህን ስላሳለፍክባቸው ሰዎች
ደፍሮ ሊናገርህ አይችልም።
15አንተ ትክክለኛ በመሆንህ፥
ዓለምን በፍትህ ታስተዳድራለች፤
በንጹሐን ላይ ቅጣትና ፍርድ፥
ከኃያልነትህ ጋር የማይሄድ ሆኖ ታየዋለህ።
16ኃያልነትህ አዳኝነትህ፥
ልዕልናህ ምሕረትህ ያጐናጽፋሉና፤
17ፍጹማዊ ሥልጣንህን ሰዎች ላለማመን ሲዳዳቸው፥
አውቀው የሚደፍሩትንም ግራ አጋባቸው።
18አንተ ግን ኃይልህን ተቆጣጥረህ፥
ፍርድህን ሚዛናዊ አድርገህ፥
ከታላቅ ምሕረት ጋር ታስተዳድረናለህ፤
አንተ ከፈቀድህ ሥልጣኑ በእጅህ ነውና።
እግዚአብሔር ለእስራኤል የጠው ትምህርት
19እንዲህ በማድረግህ ሕዝብህን አስተማርህ፤
ጻድቅ ሰው ለሌሎች ደግ መሆን እንዳለበት ገለጽህ፤
ለልጆችህ መልካም ተስፋን፥
ለኃጢአታቸውም ንስሐን ሰጠሃቸው።
20ሞት የተፈረደባቸው ቢሆንም እንኳ፥
የልጆችህን ጠላቶች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታና
በላላ መልክ ከቀጣህ፥
ከክፋትም ይርቁ ዘንድ ጊዜና ቦታን ከሰጠሃቸው፥
21ለአባቶቻቸው በመሐላ፥ በቃል ኪዳንና በተስፋ ቃል
የገባህላቸውን ሰዎች ዘሮችና ያንተን ልጆች
ትክክለኛውን ትኩረት ሰጥተህ ያልፈረድከው
ስለምንድን ነው?
22ስለዚህ በጠላቶቻችን ላይ ቅጣትህን ባለማክበድህ፥
እኛም በፍርዳችን ላይ ያንተን ደግነት
እናስብ ዘንደ አስተማርኸን፤
ለፍርድም በቀረብን ጊዜ ምሕረትህን እንጠባበቃለን።
ደረጃ በደረጃ በግብጻውያን ላይ የወረደው ቅጣት
23ከንቱና ክፋት የተሞላበት ሕይወት የሚመሩ ሰዎች
በገዛ ራሳቸው መጥፎ ተግባር እንዲሠቃዩ ያደረግኸውም ለዚሁ ነው።
24በስሕተት መንገድ ብዙ ተጉዘዋል፤
መርዘኞቹንና የጠሉትን እንስሳት በማምለክ፥
ክፉና ደጉን እንዳልለዩ ለጋ ሕፃናትም ታልለዋልና።
25አንተም ምንም እንደማያውቁ ሕፃናት
የሰው መሳቂያ በማድረግ ቀጣሃቸው።
26ከተሳልቆው ተግሣጽ ያልተማሩ ግን
የእግዚአብሔርን ታላቅ ፍርድ በቶሎ ይቀበላሉ።
27እነርሱን ያሰቃያቸው፥
አቤቱታቸውን ያቀረቡባቸው፥
አምላኮቻቸው ያደረጉአቸው እነኛው ፍጡራን፥
የቀጧቸውም እነርሱ መሆናቸውን በእውነተኛው ብርሃናቸው ተመልክተዋል፤
እስከ አሁን ድረስ አናውቅህም ያሉትን ጌታ
እውነተኛው አምላክ እንደሆነ አወቁ፤
የመጨረሻውም ቅጣት በእነርሱ ላይ ወደቀ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ