መጽሐፈ ጥበብ 11
11
1 #
ዘፀ. 15፥22—17፥16። በአንድ ቅዱስ ነቢይ ሥራቸው እንዲቃናላቸው አደረገች
2የሰው እግር ባልደረሰበት ስፍራ፥ ድንኳኖቻቸውን ተከሉ።
3ጠላቶቻቸውን በጽናት ተቋቋሙ ተቀናቃኞቻቸውንም አባረሩ።
የመጀመሪያው ተቃርኖ የውሃው ተአምር
4በተጠሙ ጊዜ ጥበብን ተጣሩ፤
ከአለታማው ገደል ውሃ፥ ከጽኑው ድንጊያ፥ የጥም ፈውስ ሰጠቻቸው።
5ጠላቶቻቸውን ለመቅጣት ያገለገሉት ሁሉ፥
በመከራ ጊዜ እነርሱን ጠቀሟቸው፤
6ጠላቶቻቸው ግን ደምና ጭቃ ተለውሶ ያደፈረሰውን የማያቋርጥ የወንዝ ምንጭ ብቻ ነበራቸው፤
7እነርሱም ሕፃናትን ለመግደል ለወጡት አዋጅ የወረደባቸው ቅጣት ነው፤
ተስፋቸው በተሟጠጠ ወቅት ውሃ በብዛት ሰጠሻቸው፤
8አንዴ በደረሰባቸው የውሃ ጥም ጠላቶቻቸውን እንዴት ክፉኛ እንደቀጣሻቸው አሳየሻቸው።
9የፍቅር እርምት ከሆነውና በራሳቸው ላይ ከደረሰው መከራ፥
በቁጣ የተፈረደባቸው ክፉዎች ሰዎች፥ ምን ያህል ስቃይ እንደ ደረሰባቸው ተገነዘቡ፤
10አባት እንደሚገሥጽ፥ አንቺም እንዲሁ የራስሽ የሆኑትን ፈተንሻቸው፤
ሌሎቹን ግን ጨካኝ ንጉሥ እንደሚሰጠው ፍርድ ዓይነት ቀጣሻቸው፤
11በዚህም ቅርብም ያሉት ሩቅ የመከራውን ገፈት እኩል ቀምሰውታል።
12ድርብ ኀዘን ደርሶባቸዋል፤ ያለፈውንም ሰቆቃ በማሰብ አቀስተዋል።
13ይደርስባቸው የነበረው ቅጣት፥ ሌሎቹን የሚጠቅም መሆኑን እንደተረዱ፥ የጌታ ሥራ መሆኑን ተገነዘቡ።
14ቀደም ሲል ያዋረዱትንና ያላገጡበትን ሰው፥ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ አደነቁት፤
ምክንያቱም በጻድቃኑ ላይ ከደረሰው እጅግ የተለየ የውሃ ጥም ስለ ደረሰባቸው ነበር።
እግዚአብሔር በግልፅ ላይ ያሳየው ትዕግስት
15 #
ዘፀ. 8፥1-24፤ 10፥12-15። አእምሮ የሌላቸውንና የሚሳቡትን፥ የተጠሉትን ጢንዚዛዎች እስከማምለክ ባደረሳቸውና
ከመንገድ ባወጣቸው ሞኝነታቸውና ክፉ ሐሳባቸው ምክንያት
ልትቀጣቸው አእምሮ የሌላቸውን የእንስሳት መንጋ ላክህባቸው።
16በዚህም የኃጢአት መሣሪያ የሆነ የቅጣትም መሣሪያ እንደሚሆን አስተማርኻቸው።
17ዓለምን ቅርጽ አልባ ከሆነው ቁስ የፈጠረው ኃያሉ እጅህ እነርሱን ለመቅጣት፥ የድብ መንጋ፥ አስፈሪ አንበሶች፥
18ወይም ያልታወቁና እንግዳ የሆኑ፥ ቁጡና እሳት የሚተፉ፥ ወይም የሚከረፋ ጢስ የሚተፋ፥ ወይም ከአይኖቻቸው አስፈሪ ብልጭታን የሚወረውሩ፥
19በጭካኔያቸው ሊያጠፍዋቸው የሚችሉትን በአውሬዎች ብቻ ሳይሆን፥ በአስፈሪ መልካቸው ሊገድሏቸው የሚችሉትንም ቢሆን፥ በእነርሱ ላይ ማዝመት አንተን የሚሳንህ ሆኖ አይደለም።
20ይሁን እንጂ ያለ አራዊቱም ቢሆን፥ በአንድ ትንፋሽ እንዲጠፉ ማድረግ አይቻል ነበርን። ተፈርዶባቸውና በኃይልህ ትንፋሽ ተበታትነው ሊቀሩ ይችሉ ነበር።
የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት
21ታላቁ ኃይልህ ሁልጊዜ በሥልጣንህ ሥር ነው፤
የክንደህን ኃይል ሊቋቋም የሚችልስ ይኖራልን
22በምድር ላይ እንደሚወድቅ የማለዳ ጤዛ ጠብታ፥
መላው ዓለምም ላንተ እንደዚሁ በሚዛን ላይ እንደሚደረግ ኢምንት ክብደት ነው።
23አንተ ግን ሁሉን ቻይ በመሆንህ፥ ምሕረትህ ለሰዎች ሁሉ ነው፤
ሰዎች ቢበድሉም ይጸጸቱ ዘንድ ታልፋቸዋለህ።
24ፍጥረቶችህን ሁሉ ትወዳለህ፤ ከፍጡራንህ አንዱን ስንኳ አትጠላም፤
ምክንያቱም ብትጠላው ኖሮ አትፈጥረውምና።
25ያለ አንተ ፈቃድ እንደምን ፍጡርህ ሊኖር ይችላል
ባንተስ ባይጠራ ኖሮ እንደምን ይጠበቃል
26የሕይወት ወዳጅ ጌታ ሆይ ሁሉም ያንተ ነውና ትጠብቀዋለህ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 11: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ