መጽሐፈ ሲራክ 7

7
ልዩ ልዩ ምክሮች
1ክፉ ነገር አታድርግ፥ ክፉ ነገር አይደርስብህም። 2ከበደል ራቅ፥ በደል ካንተ ይርቃል። 3ልጄ ሆይ በግፍ ትልሞች አትዝራ፥ ሰባት ጊዜ እጥፍ ታጭዳቸዋለህና። 4ከእግዚአብሔር ታላቅ ሥልጣንን፥ ከንጉሥ የክብር መንበርን አትጠይቅ፤ 5በእግዚአብሔር ፊት አትመጻደቅ፤ በንጉሡም ፊት ጥበበኛ ነኝ አትበል። 6በዳኝነት ለመመረጥ አታስብ፥ የፍትሕን መዛባት ላታስወግድ ትችላለህና፤ ምክንያቱም ሹም ተፅዕኖ ሊያደርግብህ ይችላል፤ የአንተም ሐቀኛነት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። 7የአገርህን ሰዎች አትበድል፤ በሕዝብህም ፊት ራስህን አታዋርድ። 8በድጋሚ አትበድል፤ ስለ አንዱም ቢሆን ከቅጣት አታመልጥምና፤ 9“እግዚአብሔር ብዙ መሥዋዕቶቼን ይመለከትልኛል፤ ለልዑል እግዚአብሔር ሳቀርባቸው ይቀበላቸዋል” አትበል። 10በጸሎትህ አታመንታ፤ መመጽወትንም አትዘንጋ፤ 11በመራራ ችግር ላይ በሚገኝ ሰው ከቶ አትሳቅ፤ ዝቅ ያደረገ አምላክ ከፍ ያደርጋልና። 12በወንድምህ ላይ ውሸትን ፈጥረህ አትናገር፤ በወዳጅህም ላይ እንደዚሁ አታድርግ። 13ምንም ጊዜ ከውሸት ተጠንቀቅ፤ ከውሸት ምንም ደግ ነገር አይገኝምና። 14በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ንግግር አታብዛ፤ በጸሎትህ ቃሎችህን አትደጋግም። 15አድካሚ ሥራን አትጥላ፤ በልዑል እግዚአብሔር የተደነገገውን የእርሻ ሥራ አትጥላ። 16ከኃጢአተኞች ጐራ አትደባለቅ፤ የእግዚአብሔር ቁጣ የማይዘገይ መሆኑን አስታውስ። 17ራስህን በጣም ዝቅ አድርግ፤ ምክንያቱም የክፉ ሰው ቅጣቱ እሳትና ትል ነው። 18ለገንዘብ ስትል ወዳጅህን፥ ለኦፊር ወርቅ ብለህ እውነተኛ ወንድምህን አትለውጥ። 19በጥበበኛዋና በመልካም ሚስትህ ላይ ፊትህን አትመልስ፤ የእርሷ ሞገስ ከወርቅ ይበልጣልና። 20በታማኝነት የሚሠራውን አገልጋይ፥ ወይም ልቡ ወደ ሥራ ያዘነበለውን የዕለት ሠራተኛ አትበድል። 21#ዘፀ. 21፥2፤ ዘዳ. 15፥12-15።አስተዋዩን አገልጋይህን ከልብህ ውደደው፤ ነጻነቱንም አትንፈገው። ልጆች 22የከብት መንጋዎች አሏችሁን? ጠብቋቸው፤ ትርፉንም ካስገኙላችሁ በሚገባ ያዟቸው፤ 23ልጆች አሉህን? አስተምራቸው፤ ከልጅነታቸው ጀምረህ አንገታቸውን እንዲደፉ አድርግ። 24ሴቶች ልጆች አሉህን? ሰውነታቸውን ተከባከብ፤ ይሁን እንጂ አታሞላቃቸው። 25ልጅህን ዳራት፥ ያኔም ታላቅ ሥራ ሠራህ። የምትድራት ግን ላስተዋይ ይሁን። ወላጆች 26በልብህ የምትወዳት ሚስት አለችህን? አታባራት፤ የማትወዳት ከሆንህ ግን አትመናት። 27#ዘፀ. 20፥12።በሙሉ ልብህ አባትህን አክብር፤ የእናትህን የምጥ ስቃይ አትርሳ። 28አንተን የወለዱህ መሆናቸውን አትርሳ፤ ላንተ ያደረጉልህን እንዴት አድርገህ ትመልስላቸዋለህ?
ካህናት
29በሙሉ ልብህ እግዝአብሔርን ፍራ፤ የሱን ካህናትም አክብር። 30በሙሉ ኃይልህ የፈጠረህን ውደድ፤ የሱን አገልጋዮችንም ቸል አትበል፤ 31እግዚአብሔርን ፍራ፤ ካህንን አክብር፤ እንደታዘዝኸው ድርሻውን ስጠው፤ የምትሰጠውም ከእህሉ የመጀመሪያውን ስለ ኃጢአት ካሣ የሚሠዋውን መሥዋዕት፥ ወርቹን፥ የመቀደሻውን መሥዋዕት ከተቀደሱት ነገሮች የመጀመሪያውን ነው።
የተቸገሩና የተጨነቁ ሰዎች
32በረከትህ ፍጹም እንዲሆን ለድሆች እጅህን ዘርጋ። 33ደግነትህ ለሕያዋን ሁሉ ይድረስ፤ ለሞቱት እንኳ ከምታደርገው አትታቀብ። 34በሚያለቅሱ ላይ ጀርባህን አታዙር፤ የኀዘንተኞችን ኀዘን ተጋራ፤ 35በሽተኞችን ከመጠየቅ ወደ ኋላ አትበል፤ እንዲህ ያለ ሥራ በመሥራትህ ተወዳጅ ትሆናለህ። 36በሥራህ ሁሉ መጨረሻህን አስታውስ፤ በኃጢአትም ከቶውን አትወድቅም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ