መጽሐፈ ሲራክ 6

6
1ወዳጅ ከሆንክ በኋላ ጠላት አትሁን፤ መጥፎ ስም እፍረትን፥ ጥላቻን ያመጣል፥ በባለ ሁለት ምላሱ ኃጢአተኛ ላይ እንደሚደርሰው ሁሉ። 2በስሜት አክናፍ አትብረር፤ ኃይልህ እንደ ኮርማ ይበታተናልና። 3ቅጠሎችህን ትበላለህ፥ ፍሬዎችህንም ታጠፋለህ፥ አንተም የደረቀ እንጨት ትሆናለህ። 4መጥፎ ባሕርይ ባለቤቱን ያጠፋል፤ የጠላቶቹ መሳቂያ ያደርገዋል። ወዳጅነት 5መልካም አነጋገር ወዳጆችን ለማፍራት ያስችላል፤ ትሕትናን የተላበሰ አንደበት ወዳጃዊ መልስን ያስገኛል፤ አማካሪህ ግን ከሺ አንድ ይሁን። 6ሰላምታ የሚሰጡህ ብዙዎች ይሁኑ፤ አማካሪህ ግን ከሺህ አንድ ይሁን። 7ወዳጅ ስትይዝ ፈትነው፤ ቶሎ ብለህ አትመነው። 8ወዳጅነቱ ለጊዜው የሆነና፤ በመከራ ቀን ወዳጅ ሆኖ የማይገኝ ሰው አለ። 9ሌላኛው ዓይነት ወዳጅ፥ ከአንተ ጋር አይሰማማም፤ ይባስ ብሎም ጸባችሁ እንዲታወቅ ያደርጋል። 10ሦስተኛው ዓይነት ወዳጅ፤ በአንድ ገበታ አብሮህ ይቀርባል፤ በመከራ ጊዜም ከአንተ ጋር አይቆምም። 11አንተን በተመቸህ ጊዜ አንተን ይሆናል፤ አገልጋዮችህንም ለማዘዝ አይፈራም። 12መከራ በወደቀብህ ጊዜ ከአንተ ይርቃል፤ ከመንገድህም ይሸሻል። 13ከጠላቶችህ ራቅ፤ ከወዳጆችህ ተጠንቀቅ። 14ታማኝ ወዳጅ ጽኑ መከታ ነው፤ እሱን ያገኘ ታላቅ ሃብትን አግኝቷል። 15ታማኝ ወዳጅ ዋጋ አይገኝለትም፤ ውድነቱም አይሰፈርም። 16ታማኝ ወዳጅ የሕይወት ቅመም ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ያገኙታል። 17እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እውነተኛ ወዳጆችን ያፈራል፤ ወዳጁም እርሱን ይመስላልና።
ጥበብን መከተል
18ልጄ ሆይ ከወጣትነትህ ጀምረህ ጥበብን ምረጥ፤ ፀጉርህ እስኪሸብት ድረስ ጥበብን ፈልጋት። 19#ያዕ. 5፥7፤8።እንደ አራሽ፥ እንደ ዘሪ ገበሬ፥ እርሷን ኮትኩታት፤ መልካም መኸሯንም ተጠባበቅ፥ እርግጥ ነው ለማረስና ለመዝራት ትደክማለህ፤ ነገር ግን በቶሎ ፍሬዋን ትበላለህ። 20ላልተገሩ ሰዎች ጥበብ ምንኛ ትከብዳለች፤ አርቀው የማያዩ ከእርሷ ጋር አይዘልቁም። 21እንደ ከባድ ቋጥኝ ትከብደዋለች፤ እርሱም እርግፍ አድርጎ ይተዋታል። 22ጥበብ በስምዋ ታማኝ ነች፤ ሁሉም የሚያገኛትም አይደለችም፤ 23ልጄ ሆይ ምክሬን ተቀበል፥ አታቃለውም፤ 24እግሮችህን በእግር ብረቷ፥ አንገትህን በአንገትዋ አስገባ። 25እርሷን ለመሸከም ትከሻህን ዝቅ አድርግ፤ በእግር ብረቷም አትበሳጭ። 26በፍጹም ልብህ ወደሷ ሂድ፤ መንገዷን በፍጹም ኃይልህ ጠብቅ። 27ፈልጋት፥ ተከተላት፤ እርሷም እራሷን ትገልጽልሀለች፤ አንዴ ከያዝካት አትልቀቃት። 28በመጨረሻ ዕረፍት በሷ ታገኛለህ፤ ስለ አንተ ደስታ ትሆንልሀለች። 29እግረ ሙቋ የማይበገር መከታ ይሆንሃል፤ አንገት ጌጥዋም የከበረ ሃብል ይሆናል። 30ቀንበርዋ የወርቅ ጌጥ ይሆንልሃል፤ ማሰሪያዎችም የከፋይ ጥብጣብ ይሆኑልሃል። 31እንደ ክቡር ካባ ትደርባታለህ፤ እንደ ደስታ አክሊልም ትቀዳጃታለህ። 32ልጄ ሆይ ከፈለግህ ትምህርትን ታገኛለህ፤ በልብህም ከተጋህ ብልህ ትሆናለህ። 33መስማትን ከወደድህ መማር ትችላለህ፤ ካዳመጥህ ጥበበኛ ትሆናለህ፤ 34በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ተገኝ፤ ብልህም ሰው ካለ ከእርሱ አትራቅ። 35ከእግዚአብሔር የመጣውን ንግግር በፈቃደኝነት አድምጥ፤ አንድም የጥበብ ምሳሌ እንዳያመልጥህ ንቃ። 36አስተዋይ ሰው ካገኘህ በማለዳ ጎብኘው፤ እግርህ የበሩን ደፍ ይመላለስ። 37#ኢያ. 1፥8፤ መዝ. 1፥2።የእግዚአብሔርን ትእዛዞች አስብ፤ ትእዛዞቹን ያለማቋረጥ አጥና፤ እሱ ራሱ ልብህን ያበረታልሃል፤ የምትሻውንም ጥበብ ታገኛለህ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ