መጽሐፈ ሲራክ 48

48
ኤልያስ
1 # 1ነገ. 17፥1-24፤ 18፥38፤ 19፥15፤16፤ 2ነገ. 1፥10-16፤ 2፥11፤ ሚል. 4፥5፤6። ነቢዩ ኤልያስ እንደ እሳት ተነሣ፤ ቃሉም እንደ ችቦ ተንቦገቦገ። 2በእነርሱ ላይ ረሃብን ያመጣ፥ ብዙዎችንም በትጋቱ ያጠፋቸው እርሱ ነው። 3በጌታ ቃል ሰማያትን ዘጋ፤ ሦስት ጊዜም እሳትን አወረደ። 4ኤልያስ ሆይ ተአምራቶች ድንቅ ናቸው፤ እንዳንተ ሊመካ የሚችል ይኖራልን? 5በልዑል እግዚአብሔር ቃል፥ ሙት ከሲኦል ስታስነሣ፥ 6ነገሠታትን ከሥልጣናቸው፥ ባለሥልጣኖችን ከግዛቶቻቸው፥ ያወረድህ አንተ ነህ። 7ተግሣጽን በሲና፥ የቅጣት አዋጅን በሆሬብ የሰማህ፥ 8ተበቃይ ነሥታትን፥ አንተን የሚተኩ ነቢያትንም የቀባህ፥ 9በእሳት ዓውሎ ነፋስ፥ በእሳታዊ ፈረሶች በማሳብ ሠረገላ የተወሰድህ፥ 10መቅሠፈቶችን ለመተንበይ፥ መዓቱ ከመውረድ በፊት፥ የእግዚአብሔርን ቁጣ ለማብረድ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው ለመመለስ፥ የያዕቆብን ነገዶች ደግሞ ለማቋቋም፥ የተመረጥህ ነህ። 11አንተን የሚያዩ፥ በፍቅር ያቀላፉ፥ የተባረኩ ናቸው፤ እኛም በእርግጥ ሕይወት ይኖረናልና።
ኤልሳዕ
12 # 2ነገ. 2፥9፤13። ኤልያስ በአውሎ ነፋስ በተከበበ ጊዜ፥ መንፈሱ በኤልሳዕ አደረ፤ በሕይወት ዘመኑ አንድም ገዥ ሊያስደነግጠው፤ አንገቱንም ሊያስደፋው አልቻለም። 13#2ነገ. 13፥20፤21።ለእርሱ የሚከብድ ነገር አልነበረም፤ ከሞተም በኋላ ትንቢት ተናግሯል። 14በሕይወት ሳለ ተአምራትን ሠርቷል፤ በሙታን ዓለምም የሚያስገርሙ ተግባራትን ፈጽሟል።
ቃል ኪዳንን ማፈረስ እና ቅጣት
15 # 2ነገ. 18፥11፤12። ይህ ሁሉ ቢደረግም ሕዝቡ አልተጸጸተም፥ ኃጢአት ከመሥራትም አልታቀበም፤ ከሀገራቸው እስኪባረሩና በምድር ሁሉ እስከተበተኑ ድረስ፥ ራሳቸውን አላስተካከሉም። 16ከዳዊት ቤት የተገኘ አንድ ሹምና፥ ጥቂት ሰዎች ብቻ ቀሩ፤ አንዳንዶቹ ግን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠሩ፤ ሌሎች ደግሞ ኃጢአትን በኃጢአት ላይ ከመሩ። 17#2ነገ. 20፥20።ሕዝቅያስ ከተማውን በምሽግ አጠናከረ፥ የውኃ ማከፋፈያም አዘጋጀ፥ ቋጥኙን በብረት ፈልፍሎ ዋሻ ሠራ፤ በዚህያም የማጠራቀሚያ ገንዳዎች ገነባ። 18#2ነገ. 18፥13-17።በእርሱ ዘመን ሴናክሬብ ወረረው፥ ራባስቴስን ላከ፥ እጁን በጽዮን ላይ አነሣ፤ በትዕቢት ተወጥሮም ደነፋ። 19ያንጊዜ ልቦቻቸውና እጆቻቸው ተንቀጠቀጡ፥ ምጥ እንደጠናባት ሴት ተጨነቁ። 20#2ነገ. 19፥15-20፤35።ነገር ግን መሐሪውን አምላክ ተማፀኑ፥ እጆቻቸውን ወደ እርሱ ዘረጉ፥ ቅዱስ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ሰማቸው፥ በኢሳይያስም እጅ አዳናቸው፤ 21እርሱ የአሞራውያንን ሠፈር አፈራረሰ፤ መልአኩም ፈጃቸው። ኢሳይያስ 22ራእዩ ጠብ በማይለው በታላቁ ነቢይ በኢሳይያስ በታዘዘው መሠረት፥ ሕዝቅያስ ጌታን የሚያስደስት ሥራ ሠራ፤ የአባቱን የዳዊት ፈለግም ተከትሎ ቆራጥነቱን አሳየ። 23#2ነገ. 20፥10፤11።በእርሱ ዘመን ፀሐይ ወደ ኋላ አፈገፈገች፥ የንጉሡንም ዕድሜ አራዘመ። 24በመንፈስ ኃይል የመጨረሻዎቹን ነገሮች ማየት ቻለ፥ የጽዮንን ኀዘንተኞች አጽናና። 25እስከ መጨረሻው ዘመን የሚሆነውን፥ የተደበቁትንም ነገሮች ከመሆናቸው አስቀድሞ ገለጸ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ