መጽሐፈ ሲራክ 46

46
ኢያሱ
1 # ኢያ. 1፥1—11፥23። የነነዌ ልጅ ኢያሱ፥ ጦረኛ፥ በትንቢትም ሥራ ሙሴን የተካ ነበር፥ እንደ ስሙ ሁሉ የሕዝብ አዳኝ በጠላቶቹ ላይ የበቀል ቅጣትን ያወረደ፥ እሥራኤልንም ለርስቱ ያበቃ ነው። 2መሣሪያውን ሲያነሣ፥ በከተሞችም ላይ ሠይፉን ሲሰነዝር ምንኛ ደስ ያሰኛል፥ 3የእርሱን ያህል ቆራጥነት ከቶ ያሳየ ይኖራልን? የእግዚአብሔርን ጦርነቶች የመራ እርሱ ነው። 4ፀሐይ የታገተቸውና አንድም ቀን ሁለት የሆነው በእርሱ እጅ አልነበረምን? 5ጠላትን በያቅጣጫው እያባረረ ሳለም ኃያሉንና ልዑል ጌታን ለመነ፥ እግዚአብሔርም ከባድና አስፈሪ በረዶን በማዝነብ መለሰለት። 6ጠላት የሆነውን ሕዝብ ወጋ፥ በቁልቁለቱም ላይ ደመሰሳቸው፥ የእርሱን ጀግንነት በጌታ ስም እንደሚዋጋ አሳያቸው።
ካሌብ
7 # ዘኍ. 14፥6-10፤ 11፥21፤ ኢያ. 14፥6-11። በሙሴ ዘመን ታማኝነቱን ያስመሰከረ፥ የኃያሉ እግዚአብሔር ተከታይ ነበር። እርሱና የዩፍኒ ልጅ ካሌብ ሕዝቡን በመቃወም፥ ኃጢአት እንዳይፈጽሙ በመጠበቅ፥ ዓመፃውንም በማብረድ ትክክለኛነታቸውን አሳይተዋል። 8ወተትና ማር ወደሚፈስባት ርስታቸውም፥ በመመለስ ላይ ከነበሩት ስድስት መቶ ሺህ ሰዎች፥ መካከል ሁለቱ ብቻ ሊድኑ የቻሉትም በጽድቅ ሥራቸው ነበር። 9ጌታ ለካሌብ እስከ እርጅናው ዘመን ያልከዳውን ብርታት ሰጠው፥ የወገኖቹ ርስት በሆነው በተራራማው ሀገርም ኃይሉን ሁሉ አዋለ። 10ጌታን መከተል መልካም መሆኑንም እስራኤላውያን ከእርሱ ይማሩ።
መሳፍንት
11 # መሳ. 1፥1—16፥31። መሳፍንቱም ሁሉ እያንዳንዳቸው ሲጠሩ፥ ልባቸው ያልሸፈተ፥ በጌታም ላይ ጀርባቸውን ያላዞሩ፥ መታሰቢያቸው የተባረከ ይሁን። 12ዓላማቸው ከመቃብራቸው በላይ ይለምልም! የነኝህ ታላላቅ ሰዎች ልጆችም፥ ያባቶቻቸውን ስም ለማደስ ያብቃቸው፤
ሳሙኤል
13 # 1ሳሙ. 3፥19፤20፤ 7፥9-11፤ 10፥1፤ 12፥3፤ 16፥13፤ 28፥18፤19። ሳሙኤል በጌታ የተወደደ ነቢይ፥ መንግሥቱንም ያቋቋመ፥ የሕዝቡንም መሪዎች የቀባ ነው። 14በጌታ ሕግ መሠረት በጉባኤው ላይ ፈርዷል፥ ጌታም ያዕቆብን ጠበቀ። 15በታማኝነቱም ነቢይነቱ ተቀባይነት አገኘ፤ በቃሉም እውነተኛ ነቢይ መሆኑን አስመሰከረ። 16በሁሉም አቅጣጫ የጠላትን መግፋት ባየ ጊዜ፥ ጡት ያልተወች ጠቦት አርዶ መሠዋዕት በማቅረብ፥ ኃያሉንና ታላቁን ጌታ ተማፀነ። 17ጌታ ከሰማይ አስገመገመ፥ ነጐድጓዳዊ ድምፁንም አሰማ፥ 18የጠላት አለቆችን፥ ፍልስጥኤማውያን መሪዎችን ሁሉ አጠፋ 19ወደ ዘላለማዊው ዕረፍቱ ከማምራቱም በፊት፥ ከማንም በላይ ቢሆን ጥንድ ጫማዎችን እንኳ አልወሰድኩም። ሲል በጌታና በመሢሑ ፊት ቃሉን ሰጥቷል፥ የከሰሰውም ሰው አልነበረም። 20ከሞተም በኋላ የንጉሡን ፍጻሜ ተንብዮአል። የሕዝቡን ኃጢአት ለማጥፋት፥ በከርሰ መቃብርም ሆኖ ትንቢት ተናግሯል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ