መጽሐፈ ሲራክ 4
4
1ልጄ ሆይ ለድኃ ለኑሮው የሚያስፈልገውን ስጠው፤ የችግረኞች ዐይኖች በምኞት እንዲቅበዘበዙ አታድርግ። 2የረሃብተኛውን ሰቆቃ አታባብስ፤ በችግር ላይ የሚገኘውን ሰው አታጥምደው። 3ለተቆጣ ልብ ጭንቅ አትጨምርበት፤ ለተቸገረ እርዳታህን አታዘግይበት። 4በጭንቅ ያለ ሰው ሲለምንህ እምቢ አትበለው፤ ፊትህን ከድሆች አትመልስባቸው። 5ችግረኛን አልመለከትም አትበል፤ ማንንም ቢሆን እንዲረግምህ ዕድል አትስጠው። 6ኑሮ የመረረው ሰው ቢረግምህ፤ ፈጣሪው እርግማኑን ይሰማል። 7በማኀበር የተወደድህ ሁን፤ በትልቅ ሰው ፊት ራስህን ዝቅ አድርግ። 8ጆሮህን ወደ ድሃ ጣል አድርገህ አዳምጥ፤ ሰላምታውንም በትሕትና መልስ፤ 9ተጨቋኞችን ከጨቋኞች እጅ አድን፤ ፍርድ ስትሰጥ ደካማ አትሁን፤ 10አባት ለሌላቸው እንደ አባት፥ ለእናቶቻቸውም ደግሞ እንደ መልካም ባል ሁን። ታዲያ አንተም ለልዑል እግዚአብሔር እንደ ልጅ ትሆናለህ፤ ፍቅሩም ከእናትህ ፍቅር የበለጠ ነው።
የጥበብ መምህርነት
11ጥበብ ልጆችዋን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ የሚፈልጓትን ትጠነቀቅላቸዋለች። 12እርሷን መውደድ ሕይወትን መውደድ ማለት ነው፤ በማለዳ የሚፈልጓትም በደስታ ይሞላሉ። 13እርሷን ያገኘ ክብርን ይወርሳል፤ በሚሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር ይባርከዋል። 14እርሷን የሚያገለግሉ ቅድሱን አምላክ ያገለግላሉ፤ እርሷን የሚወዷትን እግዚአብሔር ይወዳቸዋል። 15እርሷን የሚታዘዝ ሕዝቦችን ይገዛል፥ እርሷን የሚከተል በሰላም ይኖራል። 16ለእርሷ የታመነ ይወርሳታል፤ የወገኖቹም ንብረት ትሆናለች። 17በመጀመሪያ በጠመዝማዛ መንገዶች ትወስደዋለች፤ ፍርሃትንና ድንጋጤን ታመጣበታለች፤ እስክታምነው ድረስ በሥርዓቷ ታጠናዋለች፤ በመከራም ትፈትነዋለች። 18በኋላ በቀጥታ ወደ እርሱ መጥታ ታስደስተዋለች፤ ምሥጢሮችዋም ትገልጥለታለች። 19ነገር ግን ከሷ ቢርቅ ትተወዋለች፤ ወደ ጥፋትም ትጥለዋለች።
ራስን ዝቅ ማድረግና ሌሎችን ማክበር
20ሁኔታዎችን አይተህ ከክፉ ነገር ተጠበቅ፤ በራስህ አትፈር። 21ወደ ኃጢአት የሚመራ እፍረት አለ፤ የሚያስከብር ሞገስም ያለው እፍረት አለ። 22በራስህ ላይ እምብዛም አትጨክን፤ እፍረት ወደ ውድቀት እንዲመራህ አትፍቀድ። 23መልካም ውጤት ያስገኛል ብለህ ካመንክ ከመናገር ወደኋላ አትበል ጥበብህንም አትደብቅ፤ 24ጥበብህ የሚታወቀው በአነጋገርህ ነውና፥ አዋቂነትህም በቃላትህ ይመሰከራል። 25እውነትን ከምትቃረን፤ በድንቁርናህ ብታፍር ይቀላል። 26ኃጢአትህን ለመናዘዝ አትፈር፤ የጅረትህን ውሃ ለማቆም አትድከም። 27በሞኝ ፊት ራስህን ዝቅ አታድርግ፤ ለኃይለኞች አትወግን፤ 28ስለ እውነት እስከ ሞት ታገል፤ እግዚአብሔር አምላክህ ከጐንህ ይዋጋል። 29በምላስህ ደፋር፥ ይልቁንም በሥራህም ሰነፈና ቸልተኛ አትሁን። 30በቤትህ አንበሳ፥ አገልጋዮችህን በተመለከተ ፊሪ አትሁን፤ 31#የሐዋ. 20፥35።ለመቀበል የሚዘረጉት እጆችህ፥ ለመስጠት አይሰብሰቡ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ