መጽሐፈ ሲራክ 37

37
ሐሰተኛ ወዳጆች
1ጓደኛ ሁሉ እኔም እኮ ወዳጅህ ነኝ ይላል፤ አንዳንዶች ግን የስም ወዳጆች ናቸው። 2ጓድህ ወይም ወዳጅህ ጠላትህ ሲሆን፥ ከልብ አያሳዝንም? 3ክፋት ሆይ! ምድርን በውስልትና ለማጥለቅለቅ ስለምን ተፈጠርህ? 4አንደኛው ዓይነት ወዳጅ በተድላ ጊዜ አብሮ ይደሰታል፥ በመከራ ወቅት ግን ይሸሻል። 5ሌላው ደግሞ ለወዳጁ ተቆርቋሪ ነው፤ በፍልሚያ ወቅት አብሮ መሣሪያ ያነሣል። 6እውነተኛውን ወዳጅ አትዘንጋ፤ ሀብት ባፈራህም ጊዜ አትርሳው።
አማካሪዎች
7አማካሪ ሁሉ ምክርን ይለግሳል፥ አንዳንዶች ግን ለፍላጐታቸው የተገዙ ናቸው። 8ምክርን ከሚሰጥ ሰው ተጠበቅ፤ እርሱ የሚሻውንም ቀድመህ እወቅ። ምክሩ የፍላጐቱ ውጤት በመሆኑ ባንተ ላይ ሊያሴር ይችላልና። 9ትክክለኛውን ፈር ተከትለሃል ይልሃል፤ ካንተ ርቆ ግን ምን እንደሚያደርስብህ ይመለክታል። 10የጐሪጥ ከሚያይህ ሰው ምክርን አትጠይቅ፤ ባንተ ከሚቀኑ ሰዎች ሐሳብህን ደብቅ። 11ሴትን ስለጣውንቷ፥ ፊሪን ስለ ጦርነት፥ ነጋዴን ስለዋጋ፥ ሸማችን ስለገበያ፥ ባለጌን ስለ ውለታ፥ ራስ ወዳዱን ስለ ደግነት፥ ሰነፉን ስለ ሥራ፥ ዳተኛውን ስለ ሥራው ፍጻሜ፥ ሀኬተኛውን አገልገይ ስለ አስቸጋሪው ሥራ አትጠይቃቸው። ከእነርሱ የሚመጣውንም ምክር አትቀበል። 12ትእዛዛትን ከሚፈጽመው ጻድቅ ሰው፥ ነፍሱ ነፍስህን ከምትመስለው ሰው፥ ብትበድል እንኳ ከሚያዝንልህ ሰው ዘንድ አትራቅ። 13ልብህ ከምትለግስህ ምክር አትውጣ፤ ከእርሷ የበለጠ ታማኝ የሚሆንህ የለምና፤ 14ማማ ላይ ከሚቆሙ ሰባት ቃፊሮች ይልቅ፥ ነፍስህ ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ትሰጥሃለችና። 15ከነኚህም ሌላ ወደ እውነት ይመራህ ዘንድ፥ ልዑል እግዚአብሔርን ለምን።
ትክክለኛና ሐሰተኛ ጥበብ
16ለማንኛውም ተግባር መሠረቱ፥ መርምር መሆን አለበት። ከማንኛውም እንቅስቃሴ በፊት፥ ማሰብ መቅደም ይኖርበታል። 17የሐሳቦች ሥረ መሠረት ልብ ነው፤ አራት ቅርንጫፎችን ያበቅላል። 18እነርሱም፥ ደግና ክፉ፥ ሕይወትና ሞት ናቸው። የሁሉም እመቤት ደግሞ ምላስ ናት። 19አንዳንዱ ሌሎቹን ለማስተማር ብቁ ነው፤ ለራሱ ግን አያውቅም። 20ንግግር አዋቂው ደግሞ የተጠላ ነው፤ መጨረሻውም በጠኔ መሞት ነው፤ 21ጥበብ የተነፈገው፥ የእግዚአብሔርንም ቸርነት ያላገኘ ነውና። 22ሌላው ራሱን አዋቂ ያደርጋል፤ በጥበቡ የሚደርስበትንም ድምዳሜ ሐቅ ነው ይላል። 23እውነተኛው ጠቢብ ግን ሕዝቡን ያስተምራል፤ የጥበብም ፍሬ ይጐመራል፤ 24ጥበበኛ ሰው ምርቃት ይጐርፍለታል፤ ያዩት ሁሉ ደስተኛ ነህ ይሉታል። 25የሰው ሕይወት ቀናቱ የተወሰኑ ናቸው፤ የእስራኤል ግን አይቆጠርም። 26ጥበበኛ ሰው በሕዝቡ ዘንድ የታመነ ነው፤ ስሙም ለዘለዓለም ሕያው ይሆናል።
መመጠን
27ልጄ ሆይ! በሕይወት ዘመንህ ለጤናህ የሚስማማህን ፈልግ፤ ለእርሱ የማይስማማውን አታቅርብለት፤ 28ሁሉም ነገር ለሁሉም ሰው ተስማሚ ሊሆኑ፥ ሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር ሊወድ አይችልምና። 29ውበትን ሁሉ አልጠግብ ባይ አትሁን። ለምግብ አትሰስት። 30ከመጠን በላይ መብላት ሕመምን፥ ገደብ የለሽም መሆን የጉበት መነካትን ያስከትላል። 31በቁንጣን ሳቢያ ብዙዎች አልቀዋል፤ ዕድሜህን ለማርዘም ራስህን ተቆጣጠር።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ