መጽሐፈ ሲራክ 24
24
የጥበብ ንግግር
1ጥበብ ራሷን ታሞግሳለች፤ በተከታዮቿም ዘንድ በራሷ ትከበራለች። 2በልዑል እግዚአብሔር ጉባኤም ትናገራለች፤ በኃያሉ አምላክ ፊት ክብርን ታገኛለች። 3እኔ ከልዑል እግዚአብሔር አፍ ወጣሁ፥ ዓለምንም እንደ ጉም ሸፈንኋት፤ 4#ዘፀ. 33፥9፤10።በሰማያት ድንኳኔን ዘረጋሁ፤ ዙፋኔም የደመና ምሰሶ ነበር። 5ብቻዬን ሰማያትን የዞርሁ፥ በጥልቁም ጉድጓድ የተጓዝሁ እኔ ነኝ። 6በባሕር ማዕበሎችና በመላዋ ምድር፥ በሕዝቦችና በሀገሮች ሁሉ ላይ ሥልጣኔ የተዘረጋ ነበር። 7በእነርሱም መካከል ላርፍ ፈለግሁ፥ ስፍሬንም የት እንደማደርግ ተመለከትሁ። 8በዚያን ጊዜ የሁሉ ነገር ፈጣሪ አዘዘኝ፥ እኔን የፈጠረኝ ለድንኳኔ ሥፍራ አዘጋጅ። ድንኳንሽን በያዕቆብ ትከይ፥ ርስትሽንም በእስራኤል አድርጊ አለኝ። 9ከሁሉ አስቀድሞ እኔን ከዘላለማዊነት ፈጠረ፤ ለዘለዓለምም እኖራለሁ። 10በተቀደሰው ድንኳን በእርሱ ፊት እገለገልሁ፤ ማደሪያዬንም በጽዮን አደረግሁ። 11በተወደደችው ከተማ አሳረፈኝ፤ ሥልጣኔንም በኢየሩሳሌም አሳየሁ። 12የአምላክ ንብረትና ውርሱ በሆኑት፥ በተመረጡት ሕዝቦች ዘንድ ሠራን ሰደድሁ። 13እንደ ሊባኖስ ዝግባ መስሎ፥ በሔርሞን ተራራ እንደሚገኘው ጥድም ታላቅ ሆንሁ። 14እንደ ኤን-ገዳ ዘንባባና፥ እንደ ኢያሪኮ ጽጌረዳም አደረግሁ፥ በሜዳ እንደ በቀለ ውብ ወይራ፥ እንደ ለውዝ ዛፍም ተንዥረገግሁ። 15እንደ ቀረፋ፥ እንደ ሜሮንም ዛፍ፥ መልካም መዓዛዬን ሰጠሁ፤ እንደ ምርጥ ከርቤ፤ እንደ ልባንጃ ጥሪኝና ኦኒካ እንደሚባል ሽቶ፥ በድንኳኑ እንደሚጨሰው ዕጣንም፥ ጣፋጭ ሽዬን ታገሥሁ። 16ቅርንጫፎቼን እንደ ቱሪማንትሪ ዘረጋሁ፤ እነርሱም ክብርና ሞገስ ያላቸው ናቸው። 17እኔ እንደሚንዠረገግ ሐረግ ነኝ፤ አበቦቼም የክብርና የሀብት ፍሬዎች ተሸክመዋል።#24፥17 18. እኔ የመልካም ፍቅር፥ የአክብሮት፥ የእውቀት፥ የተቀደሰ ተስፋ እናት ነኝ፤ በእርሱ ለተጠሩ ለልጆቼ ሁሉ ዘላለማዊነትን እሰጣለሁ። 19የምትፈልኝ ቅረቡኝ፤ ክፍሬዎቼም ያሻችሁን ያክል ውሰዱ። 20ትዝታዬ ከማር ይጣፍጣል፤ እኔን መውረስ ከማር ወለላ ይመረጣል። 21እኔን የሚመገቡ ይበልጥ ይራባሉ፤ እኔን የሚጠጡ ይበልጥ ይጠማሉ። 22ትእዛዜን የሚፈጽም አያፍርም፤ እኔ የማዘውን የሚያደርግ ከቶውንም ኃጢአት አይሠራም።
ጥበብና ሕግ
23ይህ ሁሉ የልዑል እግዚአብሔር የቃል ኪዳን መጽሐፍ ነው። ለእኛ ለያዕቆብ ቤተሰቦች በሙሴ አማካኝነት የተሰጠን ሕግ ነው።#24፥23 24. በጌታ እርዳታ ታምናችሁ ተስፋ አትቁረጡ፤ ነገር ግን በምትችሉት መጠን ይልቅ የተጋችሁ ሁኑ። ሁሉን ቻይ ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ከእርሱ ሌላም የሚያድን የለም። 25ጥበብን እንደ ፌቮን፥ በፍሬ ወቅት እንደሚፈሰው የጤግሮስ ወንዝ የሚያጥለቀልቃት፥ 26እውቀትን እንደ ኤፍራጥስ፥ በመከር እንደሚሞላው የዮርዳኖስ ወንዝ የሚያጥለቀልቃት፥ 27ምክርንም እንደ ዓባይ የሚያፈስ፥ በወይን ለቀማ ወቅት እንደ ግዮን የሚያንዠረዥረው የሙሴ ሕግ ነው። 28የመጀመሪያው ሰው ጠንቅቆ ሊያውቃት አልቻለም፤ የመጨረሻውም አላገኛትም። 29ሐሳብዋ ከባሕር የሰፋ፥ ትልሟም ከጥልቅም ጥልቅ ነውና። 30እኔም እንደ መስኖ ቦይ፥ ወደ አትክልት ሥፍራም እንደሚፈስ የውሃ መስመር፥ 31አትክልቱን ውሃ አጠጣለሁ፤ አበባዎቼን በመስኖ አለማለሁ አልሁ፤ እነሆ መስኖዬ ወንዝ፥ ወንዜም ባሕር ሆነ። 32ከንጋት ጀምሮ ምክር እንዲያበራ፥ ብርሃኑንም በስፋትና በርቀት እንዲፈነጥቅ አደርጋለሁ። 33ትምህርት እንደ ትንቢት፥ የወደፊት ትውልዶች ውርስ ይሆን ዘንድ እጥራለሁ። 34እነሆ አስተውሉ! ለግሌ ብቻ ሳይሆን ጥበብን ለሚሹ ሁሉ ስል ደክሜያለሁ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 24: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ