መጽሐፈ ሲራክ 20

20
ዝምታና ንግግር
1ያ ጊዜው የሚሰነዘር ተግሣጽ አለ፤ ዝምተኛ ሰው አለ፥ እርሱም ብልጥ ነው። 2በቁጣ ከመንደድ መገሠጽ ምንኛ የተሻለ ነው! 3ጥፋቱን የሚያምን ከቅጣት ይድናል። 4ፍትሕን በኃይል ለመጫን የሚሻ ሰው፥ ልጃገረድን ለመድፈር እንደሚሞክር ጃንደረባ ነው። 5ዝምተኛ ሰው እንደ ጥበበኛ ይቆጠራል፤ ብዙ በመናገሩ ደግሞ የሚጠላ ሰው አለ። 6አንዳንዱ ሰው መልስ ስለሌለው ዝም ይላል፤ ሌላው ደግሞ መች እንደሚናገር ስለሚያውቅ ዝም ይላል፤ 7ወቅቱ እስኪደርስ ብልህ ሰው በዝምታው ይቀጥላል፤ ለፍላፊው ሞኝ ግን ይህን አይረዳም። 8ብዙ የሚናገር ይጠላል፥ የማይገባውን ሥልጣን የያዘም ሰው አይወደድም።
ተፃራሪ አባባሎች
9አንዳንዱን መከራ ይጠቅመዋል፤ ዕድላምነቱም ያከስረዋል። 10ምንም ጥቅም የማይሰጥ አንዳንድ ስጦታ አለ፤ እጥፍ ድርብ ጥቅም የሚያስገኝ ስጦታም አለ፤ 11አንዳንድ ጊዜ ክብር ለውርደት ይዳርጋል፤ የተዋረዱም ሰዎች እራሳቸውን ያቀናሉ። 12አንዳንድ ሰው በጥቂት ገንዘብ ብዙ ነገሮች ይበዛል፤ ሆኖም ግን ሰባት እጥፍ ይከፍልበታል። 13ጥበበኛው በቃሉ ይፈቀራል፥ አላዋቂው ግን በከንቱ ስጦታዎችን ያፈሳል። 14የአላዋቂ ሰው ሰጦታ ምንም አይጠቅምህም፤ ዐይኖቹ ሰባት ጊዜ እጥፍ ምላሽን ይጠብቃሉበና። 15ጥቂት ይሰጣል፤ ብዙ ይነቅፋል፤ እንደ አዋጅ ነጋሪ አፉን በሰፊው ይከፍታል። ዛሬ አበድሮ በነጋታው ክፍያን ይጠይቃል፤ እንዲህ ያለ ሰው በጣም የተጠላ ነው። 16ሞኝ ወዳጅ የለኝም፤ በመልካም ሥራዎቼ የሚያመሰግነኝ ማንም የለም፤ 17እንጀራዬን የሚበሉ ሰዎች ነገረኛ ምላስ አላቸው ይላል። ስንቴ በስንቶቹ ይሳቅበት ይሆን!
የማይገባ ንግግር
18ምላስ ከሚያዳልጥ በመንገድ ዳር መውደቅ ይሻላል፤ ኃጢአተኞች ሳያስቡት የሚወድቁት እንዲሁ ነው። 19ያልታረመ ደንቆሮ ሰው ደጋግመው እንደሚያወሱት ታሪክ ውል የሌለው ነው። 20ሞኝ በተገቢው ወቅት የማይናገር በመሆኑ፤ ከእርሱ የሚመነጭ ምሳሌም ተቀባይነትን አያገኝም። 21ማጣት ከኃጢአት የሚጠብቀው ሰው አለ፤ የሕሊና ጸጸትም ዕረፍት አይነሳውም። 22እውነተኛ ካልሆነ ዕረፍት በመነሣት በራስ ላይ ጥፋትን የሚጋብዝ አለ፤ ስለ ሞኞቹ አስተያየት ሲል እንዲሁ የሚጠፋ አለ። 23እውነተኛ ያልሆነ ዕረፍት ለወዳጅ የተስፋ ቃል የሚሰጥና ሳይቸግረው ጠላት የሚገዛም አለ።
መዋሸት
24መዋሸት በሰው ላይ የሚሳፍር ዕድፍ ነው፤ ባልተገራ አፍ ላይ ሁልጊዜ ውሸት ይገኛል። 25ልማደኛ ዋሾ ከመሆን ይልቅ ሌባ መሆን ይሻላል፥ ሁለቱም ግን የሚያመሩት ወደ ጥፋት ነው። 26ውሸት የሚጠላ ባሕሪ ነው፤ የውሸታም ውርደት ዘላለማዊ ነው።
ጥበብ
27ጥበበኛ የሚሻሻለው በቃላት ነው፤ ብልጥ ደግሞ በታላላቆች ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል። 28መሬቱን የሚያርስ መኸሩን ያፍሳል፤ ከታላላቆች ዘንድ የተጠጋ ስለጥፋቱ ይቅርታን ያገኛል። 29እጅ መንሻና መማለጃ ስጦታ የጥበበኞችን ዐይን ይሸፍናል፤ ተግሣጽንም በአፍ ላይ እንደተደገነ አፈ ሙዝ ያፍናል። 30ጥበብ ከተደበቀ፥ ሀብትም ካልታወቀ፥ የሁለቱስ ቢሆን ጥቅማቸው ከምኑ ላይ ነው? 31ጥበቡን ከሚደብቅ ሰው፥ ሞኝነቱን የሚሸፍን ሰው ይበልጣል።#20፥31 ጌታን በሚያገለግልበት ጊዜ ነፍስን ለመጠበቅ ላልተገራ መሪነት ይልቅ የማይቀረውን ጊዜ መጠበቅ የተሻለ ነው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ