መጽሐፈ ሲራክ 18
18
የእግዚአብሔር ታላቅነት
1ዘላለማዊው አምላክ ሁሉንም ፈጠረ፥ ትክክለኛውም ዳኛ እርሱ ብቻ ነው። 2ጻድቅ የሚባል እግዚአብሔር ብቻ ነው።#18፥2 3. ያለ እርሱ ሌላ የለም። ዓለምን ይመራል፤ ሁሉም ነገር የእርሱን ፈቃድ ይታዘዛል፤ የሁሉም ንጉሥ ነውና በኃይሉ የተቀደሱ ነገሮች ከርኩስ ነገሮች ይለያል። 4ለማንም ቢሆን ሥራዎቹን ሁሉ የማወቅን ሥልጣን አልሰጠም፥ ድንቅ ሥራዎቹንስ ሊመረምር የሚችል ማን ነው? 5ወሰን የሌለው ኃያልነቱን የሚገመግም ማን ነው። ስለ ምሕረቶቹስ ዘልቆ መናገር የሚችልስ አለን? 6ከምሕረቱ ላይ መቀነስ ወይም መጨመር አይቻልም፤ የጌታን ተአምራት ጠልቆ ለማየት አይሞከርም። 7ሰው ጨረስኩ ሲል ገና መጀመሩ ነው፤ ምርምሩንም ሲያበቃ፥ እንቆቅልሹ ሲጀምር እንደነበረው ነው።
የሰው ከንቱነት
8ሰው ምንድነው? ለምንስ ይጠቅማል? የሚጠቅመውና የሚጐደውስ ምንድነው? 9የሕይወቱ ርዝማኔ ቢበዛ መቶ ዓመት ነው። 10ከዘላለማዊነት ጋር ሲነጻጸሩ እኒህ ዓመታት ከባሕር እንደ ተገኘ ውሃ ጠብታ ወይም እንደ አንዲት አሸዋ ይቆጠራል። 11ስለዚህ ነው እግዚአብሔር ለሰዎች ትዕግሥተኛ የሆነውና ርኀራኄውንም የሚያደርግላቸው። 12የሰውን ልጆች ፍጻሜ አስከፊነት የሚያውቀውና የተገነዘበው በመሆኑ፥ ይቅርታውን ያበዛል። 13የሰው ርኀራኄ ለባልንጀራው ነው፤ እግዚአብሔር ግን ለፍጥረት ሁሉ ይራራል፥ ይገሥጻል፥ ያርማል፥ ያስተምራል፥ እረኛ መንጋውን እንደሚመልስ፥ እሱም ወደ መንገድ መልሶ ያገባል። 14ምክሩን ለሚቀበሉና ውሳኔውን በትጋትና በጥንቃቄ ለሚፈልጉ ሰዎች ይራራላቸዋል።
የመስጠት ጥበብ
15ልጄ ሆይ ነቀፌታ የሚያስከትለውን ደግ ነገር አድርግ፤ በስጦታዎችህ ላይ አሳዛኝ ቃላት አታደባልቅ። 16ጤዛ ሙቀትን አይቀንስምን? ቃልም እንደዚሁ ከስጦታ ይልቃል። 17በርግጥም መልካም ቃል ከታላቅ ስጦታ የተሻለ ነው፤ ቸር ሰው ግን ሁለቱንም ለመስጠት ዝግጁ ነው። 18አላዋቂ ሰው ቢያቀርብም ዘለፋን ነው፤ የሚያስቆጭ ስጦታ ደግሞ ዐይኖችን ያስለቅሳል።
ማሰላሰልና አርቆ መመልከት
19ከመናገርህ በፊት ተማር፥ ከመታመምህ በፊት ተጠንቀቅ። 20ከፍርድ ቀን በፊት እራስህን መርምር፥ በጉብኝቱም ቀን ነጻ ትሆናለህ። 21ከመታመምህ በፊት ትሕትናን ተላመድ፥ ኃጢአት እንደፈጸምክ ተጸጸት። 22ቃል ከመግባትህ በፊት እራስህን አዘጋጅ፤ እግዚአብሔርን እንደሚያስቀይሙት ሰዎች አትሁን፤ 23ቃል ከመግባትህ በፊት እራስህን አዘጋጅ፤ ጌታን እንደሚፈታተኑት ሰዎች አትሁን፤ 24በመጨረሻው ቀን የሚመጣውን ቅጣት አስታውስ፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወዲያ ሲመልስ የሚወርደውን ቁጣ አስብ። 25በጥጋብ ጊዜ የራብ ዘመንን አስታውስ፤ ሀብታምም ባትሆን ድኀነትንና ማጣትን አስብ። 26ንጋትና ምሽት ሲፈራረቁ ጊዜው ያለፋል፤ ላምላካችን ሁሉም ቶሎ ያልፋል። 27ጥበበኛ ሰው በሁሉ ነገር ይጠነቀቃል፤ እግዚአብሔርን ላለማስቀየምም፥ በበደል ወቅቶች እራሱን ይጠብቃል። 28አስተዋይ ሰው ሁሉ ጥበብን ያውቃታል፤ እርሷንም ያገኘውን ያከብራል። 29ያነጋገር ለዛዎችን የሚገነዘቡ፥ ስለ ጥበብ ተግተው ሠርተዋል፤ ትክክለኛ ምሳሌዎችንም አንቆርቁረዋል።
ራስን መግዛት
30ለስሜቶችህ ተገዢ አትሁን፥ ፍላጎቶችህንም ግታ። 31ፍላጎቶችህን ካረካህ፥ የጠላቶችህ መሳቅያ ትሆናለህ። 32በምቾት ኑሮ አትንደላቀቅ፥ ከዚህም ማኀበር አትደባለቅ። 33ኪስህ ባዶ ሆኖ በብድር ብትፈነጭ፥ እራስክን ታደኸያለህ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 18: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ