መጽሐፈ ሲራክ 10
10
መስተዳድር
1ጥበበኛ ገዢ ሕዝቡን ያስተምራል፤ ተከታዮንም ሥርዓት ያስተምራል። 2ዳኛው እንደ ሆነው ባለሥልጣናቱም ይሆናሉ፤ የከተማው ገዢ እንደ ሆነው ነዋሪዎቹም ይሆናሉ። 3አላዋቂ ንጉሥ የሕዝቡ ጥፋት ነው፤ የአንዲት ከተማ ብልጽግና በመሪዎቿ አስተዋይነት ይወሰናል። 4የምድር አስተዳደር በእግዚአብሔር እጅ ነው፥ በትክክለኛው ወቅት ሁነኛ መሪ ያስነሣላታል። 5የሰው ሥራ መቃናት በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ክብሩን የሚያሳርፈው የሕግ መምህር በሆነው ሰው ላይ ነው። 6በባልንጀራህ ላይ በምንም ዓይነት በበደሉ ቂም አትያዝበት፥ በቁጣ ተነሣሥተህ ምንም ነገር አታድርግ። በበደሉ ቂም አትያዝበት፤ በቁጣ ተነሣሥተህ ምንም ነገር አታድርግ። 7ትዕቢት በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ዘንድ የተጠላ ነው፤ ፍትሕን ማጓደል በሁለቱም ዘንድ የተወገዘ ነው። 8ፍትሕን በማዛባት በንዋይ የተነሣ ነጻነት፥ ከአንድ ሕዝብ ወደ ሌላ ሕዝብ ይዛወራል። 9አፈርና አመድ የሆነ ሰው ስለምን ይታበያል? እሱ ገና በሕይወቱ ሳለ የሆድ ዕቃው የበሰበሰ ነው። 10የቆየ በሽታ ሐኪሙን ያቄላል፤ የዛሬ ንጉሥ የነገ አስክሬን ነው። 11በሞትም ጊዜ ከፊሉ ሥጋችን ነፍሳት፥ አራዊትና ትሎች ይሆናሉ። 12የትዕቢት መነሻው እግዚአብሔርን መክዳት፥ ልቦናንም ከፈጣሪ ማራቅ ነው። 13የትዕቢት መጀመሪያው ኃጢአት በመሆኑ፥ በሱ የሚጸና አሰቃቂ ጥፋት ይመጣበታል፥ እግዚአብሔርም በነኝህ ሰዎች ላይ ያልታሰበ ቅጣትን ያወርዳል፥ ያጠፋቸውማል። 14#1ሳሙ. 2፥8፤ ሉቃ. 1፥52።እግዚአብሐር ኃያላንን፥ ልዑላንን ከዙፋናቸው ገርስሷል፤ በምትካቸውም ትሑታንን አስቀምጧል። 15እግዚአብሐር ትዕቢተኞችን ከሥራቸው መነገለ፤ በነሱ ቦታ የበታቾቹን ተከለ። 16እግዚአብሔር የሕዝቦችን ምድር ገለባበጠ፥ እስከ መሠረታቸው ደመሰሳቸው፤ 17ከሰዎች መካከል አውጥቶ ጣላቸው፥ አጠፋቸው፥ መታሰቢያቸውንም ፋቀ፥፥ 18ትዕቢት ለሰው ልጆች፥ ቁጣም ከሴት ለተወለዱ አልተፈጠረም፤
ክብር የሚገባቸው ሰዎች
19የትኛው ዘር ነው ክብር የሚገባው? ክብር የሚገባው የሰው ዘር ነው። ክብር የሚገባው የትኛው ዘር ነው? ክብር የሚገባው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነው። መወገዝ የሚገባው የትኛው ዘር ነው? የሰው ዘር ነው። መወገዝ የሚገባው ዘር የትኛው ነው? የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያፈርሰው ነው። 20ሹም በወንድሞቹ መካከል ይከበራል፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ በእግዚአብሔር ዘንድ ይከበራሉ። #10፥20 አንዳንድ ብራናዎች እንደ ቍጥር ሃያ አንድ ያነቡታል። 22ባለጸጎች፥ ታላላቅ ሰዎች፥ ድሆች፤ እግዚአብሔርን በመፍራታቸው ሊመካ ይገባል። 23ዕውቀት ያለውን ድሃ መስደብ ደግ አይደለም፤ ኃጢአተኛን ማክበር የተገባ አይደለም። 24ባለጸጎች፥ ዳኞች፥ ገዢዎች ሁሉ ክብር ይገባቸዋል፤ እግዚአብሔርን ከሚፈራ የበለጠ ታላቅ ሰው ግን የለም። 25ብልህ አገልጋይ የሚያገለግሉትን ነጻ ሰዎች ይኖሩታል፤ አዋቂም ሰው ቅር አይሰኝም።
ግልጽነትና ትሕትና
26ሥራህን በምትሠራበት ጊዜ ብዙም አትራቀቅ፤ በመከራ ጊዜ እንዲሁ አትኰፈስ፤ 27ጠንክሮ በመሥራት ፍላጎቱን ማሟላት የቻለ፤ ላንዴ እንኳን የሚበላው ከሌለው ትምክህተኛ ይሻላል። 28ልጄ ሆይ በራስህ አትመጻደቅ፥ ስለ ራስህም ተገቢው ግምት ይኑርህ። 29እራሱን የሚጎዳውን ማን ይቀበለዋል? እራሱንስ የሚጠላውን ማን ያከብረዋል? 30ደሃ በዕውቀቱ፥ ሀብታም በሀብቱ ይከበራል። 31በድህነቱ የከበረ በጸጋ ቢሆንማ ኖሮ፤ ምን ያህል በላቀ፤ በሀብቱ ያልተከበረ ቢደኸይማ ምን ይሆን ነበር፤
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ