መጽሐፈ ምሳሌ 8:17-36

መጽሐፈ ምሳሌ 8:17-36 መቅካእኤ

እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል። ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፥ ብዙ ሀብትና ጽድቅም። ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፥ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር። እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥ በፍርድም ጎዳና መካከል፥ ለሚወድዱኝ ርስት አወርሳቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም እሞላ ዘንድ። ጌታ የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ። ከጥንቱ ከዘለዓለም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር፥ የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር። ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥ ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥ የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፥ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥ ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ። አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፥ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው። ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም። የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ። እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና። ከጌታም ሞገስን ያገኛልና። እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጐዳል፥ የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።”