ምሳሌ 8:17-36

ምሳሌ 8:17-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ እኔንም የሚሹ ሞገስን ያገኛሉ። ብልጥግናና ክብር ብዙ ሃብትና ጽድቅም በእኔ ዘንድ አሉ። ከወርቅና ከከበረ ዕንቍ ይልቅ እኔን መምረጥ ይሻላል፥ ፍሬዬም ከጠራ ብር ይሻላል። እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥ በፍርድ ጎዳና መካከልም እመላለሳለሁ፥ ለሚወድዱኝ ሀብትን እከፍላቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም በመልካም ነገር እሞላ ዘንድ። የሚሆነውን ነገር በየቀኑ ብነግራችሁ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ቍጥር አስባለሁ። እግዚአብሔር ለሥራው የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ፥ ምድርን ሳይፈጥር አስቀድሞ ከዓለም በፊት ሠራኝ፥ ቀላያትን ሳይፈጥር፥ የውኃ ምንጮችም ሳይፈልቁ፥ ተራሮች ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ፥ እግዚአብሔር ከሰማይ በታች የሚታደርባቸውን ሀገሮችንና ዳርቻዎችን ሳይፈጥር። ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ ዙፋኑን በነፋሳት ላይ ባጸና ጊዜ፥ ደመናትን በላይ ባጸና ጊዜ፥ የቀላያትን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ፥ እኔ ከእርሱ ጋር እሠራ ነበር፤ ደስም አሰኘው ነበር፥ በየዕለቱ ሁልጊዜ በፊቱ ደስ ይለኝ ነበር። ዓለምንም ፈጥሮ በፈጸመና ደስ ባለው ጊዜ፥ ደስታዬ በሰው ልጆች መካከል ነበር። አሁንም ልጄ ሆይ፥ ስማኝ፥ መንገዴን የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው። ጥበብን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸልም አትበሉት። የሚሰማኝ ሰው ብፁዕ ነው፥ መንገዴን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው፥ ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ። መንገዶቼ የሕይወት መንገዶች ናቸውና። እኔን ያገኘ ሕይወትን አገኘ፤ ፈቃዱም በእግዚአብሔር ዘንድ ይዘጋጃል። በእኔ ላይ በደልን የሚፈጽሙ ራሳቸውን ይበድላሉ፤ የሚጠሉኝም ሞትን ይወድዳሉ።

ምሳሌ 8:17-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሚወድዱኝን እወድዳቸዋለሁ፤ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል። ሀብትና ክብር፣ ዘላቂ ብልጽግናና ስኬት በእኔ ዘንድ አሉ። ፍሬዬ ከንጹሕ ወርቅ ይበልጣል፤ ስጦታዬም ከነጠረ ብር። እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፤ በፍትሕም ጐዳና እጓዛለሁ፤ ለሚወድዱኝ ብልጽግና እሰጣለሁ፤ ግምጃ ቤታቸውንም እሞላለሁ። “እግዚአብሔር ከቀድሞ ሥራዎቹ በፊት፣ የተግባሮቹ መጀመሪያ አድርጎ አመጣኝ፤ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ፣ ከጥንት ከዘላለም ተሾምሁ። ከውቅያኖሶች በፊት፣ የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው በፊት ተወለድሁ፤ ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣ ከኰረብቶችም በፊት ተወለድሁ፤ ምድርን ወይም ሜዳዎቿን፣ ወይም ምንም ዐይነት የዓለም ትቢያን ከመፍጠሩ በፊት እኔ ተወለድሁ። ሰማያትን በዘረጋ ጊዜ፣ በውቅያኖስ ላይ የአድማስ ምልክት ባደረገ ጊዜ እኔ እዚያ ነበርሁ፤ ደመናትን በላይ ባጸና ጊዜ፣ የውቅያኖስን ምንጮች በመሠረተ ጊዜ፣ ለባሕር ድንበርን በከለለ ጊዜ፣ ውሆችም የርሱን ትእዛዝ እንዳያልፉ፣ የምድርንም መሠረቶች ወሰን ባበጀ ጊዜ፣ በዚያ ጊዜ ከጐኑ ዋና ባለሙያ ነበርሁ። ሁልጊዜ በፊቱ ሐሤት እያደረግሁ፣ ዕለት ተዕለት በደስታ እሞላ ነበር፤ የርሱ በሆነው መላው ዓለም ሐሤት እያደረግሁ፣ በሰው ልጆች ደስ እሰኝ ነበር። “እንግዲህ፣ ልጆቼ ሆይ፤ አድምጡኝ፤ መንገዴን የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው። ምክሬን አድምጡ፤ ጥበበኞች ሁኑ፤ ቸልም አትበሉት። ብፁዕ ነው፤ በየዕለቱ ደጃፌ ላይ የሚጠብቅ፣ በበራፌ ላይ የሚጠባበቅ፣ የሚያዳምጠኝ ሰው፤ የሚያገኘኝ ሁሉ ሕይወትን ያገኛልና፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ሞገስን ይቀበላል። የሚያጣኝ ሁሉ ግን ራሱ ይጐዳል፤ የሚጠሉኝም ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።”

ምሳሌ 8:17-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እኔ የሚወዱኝን እወዳለሁ፤ የሚፈልጉኝም ያገኙኛል። ብልጽግናና ክብር በእኔ ዘንድ ይገኛሉ፤ ዘላቂ ሀብትና ዕድገት የእኔ ናቸው። ከእኔ የምታገኙት ጥቅም ዘላቂ ሀብትና ዕድገት የእኔ ናቸው። ከንጹሕ ወርቅና ከተነጠረ ብር የሚሻል ነው። የእኔ መንገድ የጽድቅ መንገድ ነው፤ እኔ የምከተለው የፍትሕን ፈለግ ነው። ለሚወዱኝ ሀብትን እሰጣቸዋለሁ፤ ቤታቸውንም በብልጽግና እሞላዋለሁ። “እግዚአብሔር ከሁሉ በፊት ፈጠረኝ፤ ከጥንት ጀምሮ የሥራው ተቀዳሚ አደረገኝ። ዓለም ከመፈጠርዋ አስቀድሞ፥ ከዘመናት በፊት ተሾምኩ። የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው፥ ውቅያኖሶችም ከመገኘታቸው በፊት ተወለድኩ። ተራራዎችና ኰረብቶች ከመመሥረታቸው በፊት ተወለድኩ። እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ ከመፍጠሩ በፊት፥ ወይም የመጀመሪያው ዐፈር እንኳ ከመፈጠሩ በፊት ተወለድኩ። እግዚአብሔር ሰማይን በዘረጋ ጊዜ፥ ጠፈርንም ከውቅያኖሶች በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ እኔ እዚያ አብሬው ነበርኩ። ደመናትን በጠፈር ባኖረበት ጊዜ፥ የውቅያኖስን ምንጭ በከፈተ ጊዜ፥ የባሕር ውሃዎች ከተመደበላቸው ስፍራ በላይ ከፍ እንዳይሉ ባዘዛቸው ጊዜ፥ የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ እኔ እዚያ አብሬው ነበርኩ። በዚያን ጊዜ እንደ ዋና ሠራተኛ ሆኜ ከእርሱ ጋር ነበርኩ። ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበር። እኔም በፊቱ እደሰት ነበር። እርሱ በፈጠረው ዓለም ደስ ይለኛል፤ በሰው ዘርም ሐሤት አደርጋለሁ። “ልጆቼ ሆይ! አድምጡኝ መንገዴን የሚከተሉ ይደሰታሉ። የምትማሩትን አስተውሉ፤ ብልኆች ሁኑ፤ ቸልም አትበሉት። እኔን የሚያዳምጥ፥ በየቀኑ በደጃፌ ላይ ተግቶ የሚገኝ፥ በቤቴ መግቢያ አጠገብ የሚጠባበቀኝ ሰው የተባረከ ነው። እኔን የሚያገኝ፥ ሕይወትን ያገኛል፤ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛል። እኔን ያጣ ራሱን ይጐዳል፤ እኔን የሚጠላም ሞትን ይወዳል።”

ምሳሌ 8:17-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል። ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፥ ብዙ ሀብትና ጽድቅም። ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፥ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር። እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥ በፍርድም ጎዳና መካከል፥ ለሚወድዱኝ ርስት አወርሳቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም እሞላ ዘንድ። ጌታ የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ። ከጥንቱ ከዘለዓለም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር፥ የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር። ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥ ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥ የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፥ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥ ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ። አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፥ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው። ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም። የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ። እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና። ከጌታም ሞገስን ያገኛልና። እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጐዳል፥ የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።”