በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በምንም ዓይነት ነገር አትጨነቁ። ከሰውም ማስተዋል ሁሉ በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ክቡር የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ምስጉን የሆነውን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም ሁሉ አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደገና ማሰብ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ተሰኝቻለሁ፤ አጋጣሚዎች አልተመቻቹላችሁም እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። ይህን ስል ስለሚያስፈልገኝ ነገር እያማረርሁ አይደለም፤ ያለኝ ነገር ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ጥቂትም ማግኘትን አውቃለሁ፤ ብዙም ማግኘትን አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ የመጥገብንና የመራብን ብዙ የማግኘትንና የማጣትን ምሥጢር ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ። ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ! ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተባበረ እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ ከአንድ ጊዜ በላይ የሚያስፈልገኝን ነገር ልካችሁልኝ ነበርና። ከጥሪታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታን ፈላጊ አይደለሁም። ነገር ግን የሚያስፈልገኝን ሁሉ ተቀብያለሁ፤ ተትረፍርፎልኛልም፤ መዓዛው ያማረ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከኤጳፍሮዲጡስ ተቀብዬ በሁሉ ተሟልቶልኛል። አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ያሟላላችኋል። ለአምላካችንና ለአባታችን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4:6-23
6 ቀናት
በዚህ የ6 ቀን ጥናት ውስጥ ፍርሃት፣ ግራ መጋባትና ጭንቀትን ለማስወገድ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር መኖር ምን ያህል ማድረግ እንደሚችል እናያለን። ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በማሳለፍና ከቃሉ በመማር እነዚህን ተግዳሮቶች እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል፣ ትኩረታችንን እንዴት እንደምናስተካክልና አስተሳሰባችንን እንደምንለውጥ እናያለን።
28 ቀናት
ባይብል ፕሮጀክት የዘወረደ ተከታታይ ትምህርቶችን ያዘጋጀው ግለሰቦች፣ ቡድኖች እንዲሁም ቤተሰቦች ዘወረደን፣ ማለትም የኢየሱስን ወደ ምድር መምጣት እንዲያከብሩ ለማነሳሳት ነው። ተስፋ፣ ሰላም፣ ሀሴት እና ፍቅር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉማቸው ምን እንደሚመስል ተሳታፊዎች እንዲያጤኑ ለማገዝ እንዲጠቅም፣ ይህ የአራት ሳምንት የጥናት እቅድ የአኒሜሽን ቪዲዮዎችን፣ አጫጭር ማጠቃለያዎችን እና ሃሳብ ጫሪ ጥያቄዎችን አካቷል። እነዚህ አራት መንፈሳዊ እሴቶች እንዴት በኢየሱስ በኩል ወደ አለም እንደመጡ ለመረዳት፣ ይህን የጥናት እቅድ ይምረጡ።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች