ትንቢተ ናሆም 3
3
የማይቀርና የማያጠራጥር ጥፋት
1ለደም ከተማ ወዮላት! በሁለንተናዋ ማታለልና ዘረፋ ሞልቶባታል፤ ንጥቂያ ከእርሷ አይርቅም። 2የጅራፍ ድምፅ፥ የመንኰራኵር ድምፅ፥ የፈረስ ኮቴ፥ የሠረገላ መንጓጓት ተሰምቶአል፤ 3ፈረሰኛው ይጋልባል፥ ሰይፍ ይንቦገቦጋል፥ ጦር ይብለጨለጫል የተገደለ ብዛት፥ የበድን ክምር፥ ሬሳው ማለቂያ የለውም፤ በሬሳቸውም ይሰናከላሉ። 4ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል፤ እርሷም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች። 5እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ ልብስሽን እስከ ፊትሽ እገልጣለሁ፤ ኅፍረተ ሥጋሽን ለአሕዛብ፥ ነውርሽንም ለመንግሥታት አሳያለሁ። 6ርኩሰትንም በላይሽ ልይ እጥላለሁ፥ እንቅሻለሁ፥ ማላገጫም አደርግሻለሁ። 7የሚያይሽም ሁሉ ከአንቺ ሸሽቶ፦ ነነዌ ወድማለች፤ ማን ያዝንላታል? አንቺን የሚያጽናኑ ከወዴት እፈልጋለሁ? ይላል።
8አንቺ በዓባይ ፈሳሾች መካከል ከተቀመጠችው፥ ውኃም በዙሪያዋ ከነበራት፥ ምሽግዋም ባሕር ከነበረ፥ ቅጥርዋም በባሕር ውስጥ ከነበረ ከኖእ አሞን ትበልጫለሽን? 9ኢትዮጵያና ግብጽ ወሰን የለሽ ኃይልዋ ነበሩ፤ ፉጥና ልብያ ረዳቶችዋ ነበሩ። 10ሆኖም ግን ተማርካ ተወሰደች፤ ሕፃናቶችዋ በመንገዶች ሁሉ ራስ ላይ ተፈጠፈጡ፤ በከበርቴዎችዋ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ታላላቆችዋም ሁሉ በሰንሰለት ታሰሩ። 11አንቺ ደግሞ ትሰክሪአለሽ፥ ትደበቂያለሽ፤ አንቺ ደግሞ ከጠላት የተነሣ መጠጊያን ትፈልጊአለሽ። 12ምሽግሽ ሁሉ የመጀመሪያውን የበሰለ ፍሬ እንደ ያዙ እንደ በለስ ዛፎች ነው፤ በሚወዛወዙ ጊዜ በሚበላው አፍ ውስጥ ይወድቃሉ። 13እነሆ፥ በመካከልሽ ያለው ሕዝብሽ ሴቶች ናቸው፤ የምድርሽ በሮች ለጠላቶችሽ በሰፊው ተከፍተዋል፥ መወርወሪያዎችሽን እሳት በልቶአቸዋል። 14ለከበባው ውኃ ለራስሽ ቅጂ፥ ምሽግሽን አጠናክሪ፤ ወደ ጭቃው ግቢ፥ ጭቃውንም ርገጪ፥ የጡብ መሥሪያ ያዢ። 15በዚያ እሳት ይበላሻል፥ ሰይፍ ይቆርጥሻል፥ እንደ አንበጣ ይበላሻል። እንደ አንበጣ ብዢ፥ እንደ አንበጣም ተባዢ። 16ነጋዴዎችሽን ከሰማይ ከዋክብት ይልቅ አበዛሽ፤ አንበጣ ተዘረጋና በረረ። 17ጠባቂዎችሽ እንደ አንበጣ፥ መኳንንቶችሽም በብርድ ቀን በቅጥር ላይ እንደ ሰፈረ የኩብኩባ መንጋ ናቸው፤ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ይበራሉ፥ ስፍራቸው የት እንደሆነ አይታወቅም። 18የአሦር ንጉሥ ሆይ፥ እረኞችህ አንቀላፍተዋል፤ መኳንንቶችህም ዐርፈዋል፤ ሕዝብህ በተራሮች ላይ ተበትነዋል፥ የሚሰበስባቸውም የለም። 19ስብራትህን የሚያሽል የለም፥ ቁስልህ የከፋ ነው፤ ወሬህን የሰሙ ሁሉ እጃቸውን በአንተ ላይ ያጨበጭባሉ፤ የማያቋርጥ ክፋትህ ያላለፈበት ማን ነውና?
Currently Selected:
ትንቢተ ናሆም 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ