የማቴዎስ ወንጌል 7:1-12

የማቴዎስ ወንጌል 7:1-12 መቅካእኤ

“እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ሳትመለከት በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ? ወይም እነሆ በዓይንህ ምሰሶ እያለ ወንድምህን ‘ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣልህ ፍቀድልኝ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ በዓይንህ ያለውን ምሰሶ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ። በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ። “ጠይቁ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል። የሚጠይቅ ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ የሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማነው? ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋልን? እንግዲህ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገርን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም! እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግና ነቢያትም ይህ ነውና።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች