የማቴዎስ ወንጌል 24:26-44

የማቴዎስ ወንጌል 24:26-44 መቅካእኤ

ስለዚህ ‘እነሆ በበረሀ አለ’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ በቤት ውስጥ ነው’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ባለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ቀናት መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይሎችም ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ነገዶች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱን ከታላቅ መለከት ጋር ይልካቸዋል፤ የእርሱን ምርጦች ከሰማያት ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ይሰበስባሉ። “ምሳሌውን ከበለስ ዛፍ ተማሩ፤ ቅርጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠሎችዋም ሲያቆጠቁጡ፥ ያንጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁም እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናልና። ከጥፋት ውሃ በፊት በነበሩት ከእነዚያ ቀናት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩና፥ የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉን እስኪወስድ ድረስ እንዳላወቁት፥ የሰው ልጅ መምጣትም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱ ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች አንዷ ትቀራለች። እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ። “ነገር ግን ይህን እወቁ፤ ባለቤት ሌባ ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች