ማቴዎስ 24:26-44

ማቴዎስ 24:26-44 NASV

“ስለዚህ፣ ‘ያውላችሁ፤ በረሓው ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘ይኸውላችሁ እልፍኝ ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል። በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ “ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናጋሉ።’ “በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤ እርሱም መላእክቱን ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋራ ይልካቸዋል፤ እነርሱም ምርጦቹን ከአራቱ ነፋሳት፣ ከሰማያት ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ይሰበስባሉ። “ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ። እንደዚሁም እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም። “ነገር ግን ስለዚያች ቀንና ሰዓት ከአብ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። ልክ በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል። በዚያ ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች። “እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤቱ ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር። ስለዚህ የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣል፤ እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች