መጽሐፈ ኢያሱ 9:1-15

መጽሐፈ ኢያሱ 9:1-15 መቅካእኤ

እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቈላማውም በታላቁ ባሕር ዳር በሊባኖስም ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ፥ ኬጢያዊ አሞራዊም ከነዓናዊም ፌርዛዊም ኤዊያዊም ኢያቡሳዊም፥ ይህን በሰሙ ጊዜ፥ ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ። የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፤ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠገነም የወይን ጠጅ አቁማዳ ጫኑ። ያረጀና የተጠጋገነ ጫማ በእግራቸው አደረጉ አሮጌም ልብስ ለበሱ፤ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ። ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ለእርሱና ለእስራኤል ሰዎች እንዲህ አሉ፦ “ከሩቅ አገር መጥተናል፤ እንግዲህ አሁን ከእኛ ጋር የቃል ኪዳን አድርጉ።” የእስራኤልም ሰዎች ኤዊያውያን እንዲህ አሉአቸው፦ “ምናልባት በመካከላችን የምትቀመጡ እንደሆነ እንዴትስ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እናደርጋለን?” ኢያሱንም እንዲህ አሉት፦ “እኛ ባርያዎችህ ነን።” ኢያሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ?” እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “ከአምላክህ ከጌታ ስም የተነሣ እጅግ ከራቀ አገር ባርያዎችህ መጥተናል፤ ዝናውንም፥ በግብጽም ያደረገውን ሁሉ፥ በዮርዳኖስ ማዶም በነበሩት በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን በአስታሮትም በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። ሽማግሌዎቻችንም በምድራችንም የሚኖሩት ሁሉ እንዲህ አሉን፦ ‘ለመንገድ ስንቅ በእጃችሁ ያዙ፥ ልትገናኙአቸውም ሂዱ እንዲህም በሉአቸው፦ “እኛ ባርያዎቻችሁ ነን፤ እንግዲህ አሁን ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ።” ’ ወደ እናንተ ለመምጣት በተነሣንበት ቀን ይህን እንጀራ ትኩሱን ለስንቅ ከቤታችን ወሰድነው፤ አሁን ግን እነሆ፥ ደርቆአል፥ ሻግቶአልም፤ እነዚህም የወይን ጠጅ አቁማዳዎች አዲስ ሳሉ ሞላንባቸው፤ እነሆም፥ ተቀድደዋል፤ መንገዳችንም እጅግ ስለ ራቀብን እነዚህ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አርጅተዋል።” የእስራኤልም አለቆች ከስንቃቸው ወሰዱ፥ የጌታንም ምሪት አልጠየቁም። ኢያሱም ከእነርሱ ጋር የሰላም ስምምነት አደረገ፥ በሕይወት እንዲኖሩም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የማኅበሩም አለቆች ማሉላቸው።