ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። ተዋጊዎቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታሰሙ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ ከዚያን በኋላ ግን ትጮኻላችሁ።” እንዲሁ የጌታን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው በዚያ አደሩ። ከዚያም በኋላ ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የጌታን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከጌታ ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሡ፥ ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ጌታ ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርሷም ያለው ሁሉ ለጌታ እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱ ረዓብ ከእርሷም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁታላችሁም። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለጌታ የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ ጌታም ግምጃ ቤት ይግባ።” ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ በቀጥታ አቅንቶ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ያዝዋት። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።
መጽሐፈ ኢያሱ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 6:8-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች