መጽሐፈ ኢያሱ 6:20-27
መጽሐፈ ኢያሱ 6:20-27 መቅካእኤ
ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ በቀጥታ አቅንቶ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ያዝዋት። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ። ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አመንዝራይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ።” ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው። ከተማይቱንም በእርሷም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ ብቻ በጌታ ግምጃ ቤት አኖሩት። ኢያሪኮንም ሊሰልሉ ኢያሱ የላካቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱን ረዓብን፥ የአባትዋንም ቤተሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርሷም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች። በዚያን ጊዜም ኢያሱ እንዲህ ብሎ ማለ፦ “ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በጌታ ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኩር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ።” ጌታም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ዝናውም በምድር ሁሉ ላይ ተሰማ።

