መጽሐፈ ኢያሱ 6:1-7

መጽሐፈ ኢያሱ 6:1-7 መቅካእኤ

ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርሷ የሚገባ ከእርሷም የሚወጣ ማንም አልነበረም። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። እናንተም ከተማይቱን ትዞሩአታላችሁ፥ ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ ከተማይቱን በቀን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ እርሷ አቅንቶ በቀጥታ ይገባል።” የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሱ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በጌታ ታቦት ፊት ይሸከሙ።” ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦ “ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ተዋጊዎቹም በጌታ ታቦት ፊት ይሂዱ።”