መጽሐፈ ኢያሱ 21:1-19

መጽሐፈ ኢያሱ 21:1-19 መቅካእኤ

የሌዋውያን አባቶች አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ነገዶች አለቆች ቀረቡ፤ በከነዓን ምድር ባለችው በሴሎ እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፦ “ጌታ በሙሴ አማካይነት የምንቀመጥባቸውን ከተሞችና ለከብቶቻችን መሰማሪያቸውን እንዲሰጠን አዝዞአል።” የእስራኤልም ልጆች እንደ ጌታ ትእዛዝ ከርስታቸው እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያን ሰጡ። ለቀዓትም ወገኖች ዕጣ ወጣ፤ ሌዋውያንም ለነበሩ ለካህኑ ለአሮን ልጆች ከይሁዳ ነገድ፥ ከስምዖንም ነገድ፥ ከብንያምም ነገድ ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ወሰዱ። ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከኤፍሬም ነገድ፥ ከዳንም ነገድ፥ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ዐሥር ከተሞች በዕጣ ወሰዱ። ለጌድሶንም ልጆች ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ወሰዱ። ለሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ ዐሥራ ሁለት ከተሞች ወሰዱ። ጌታም በሙሴ አማካይነት እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያን በዕጣ ሰጡ። ከይሁዳም ልጆች ነገድ ከስምዖንም ልጆች ነገድ በስማቸው የተጠሩትን እነዚህን ከተሞች ሰጡ። የፊተኛው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣ የሌዊ ልጆች የቀዓት ወገን ለሆኑ ለአሮን ልጆች ሆኑ። በይሁዳ ተራራማ አገር ያለችውን ቂርያት-አርባቅ የምትባለውን ከተማ በዙሪያዋም ያለውን መሰማሪያ ሰጡአቸው፤ እርሷም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። የከተማይቱን እርሻ ግን መንደሮችዋንም ለዮፎኔ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት። ለካህኑም ለአሮን ልጆች እነዚህን ሰጡ፤ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ኬብሮንና መሰማሪያዋን፥ ልብናንና መሰማሪያዋን፥ የቲርንና መሰማሪያዋን፥ ኤሽትሞዓንና መሰማሪያዋን፥ ሖሎንንና መሰማሪያዋን፥ ዳቤርንና መሰማሪያዋን፥ ዓይንንና መሰማሪያዋን፥ ዮጣንና መሰማሪያዋን፥ ቤት-ሳሜስንና መሰማሪያዋን፤ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገዶች ዘጠኝ ከተሞችን ሰጡ። ከብንያምም ነገድ ገባዖንንና መሰማሪያዋን፥ ናሲብንና መሰማሪያዋን፥ አናቶትንና መሰማሪያዋን፥ አልሞንና መሰማሪያዋን፤ አራት ከተሞችን ሰጡ። የአሮን ልጆች የካህናት ከተሞች ሁሉ ከመሰማሪያቸው ጋር ዐሥራ ሦስት ከተሞች ናቸው።