“አሁንም ተጣራ፥ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ? አላዋቂውን ሰው ቁጣ ይገድለዋል፥ ሞኙንም ቅንዓት ያጠፋዋል። አላዋቂውን ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ። ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥ የሚደርስላቸውም የለም። የሰበሰበውንም የተራበ ይበላዋል፥ ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፥ የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ። ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፥ ሰው ለመከራ ተወልዶአል የአሞራ ግልገሎች ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንደሚሉ። እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር። የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል። በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል። የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ ያዘኑትን ለደኅንነት ከፍ ያደርጋቸዋል። የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል፥ እጃቸውም ደባቸውን ከግብ እንዳያደርስ። ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፥ የጠማሞችንም ምክር ያጠፋል። በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ። ድሀውን ከአፋቸው ሰይፍ አንዲሁም ከኃያላን እጅ ያድነዋል። ለምስኪኑም ተስፋ አለው፥ ግፍ ግን አፍዋን ትዘጋለች። እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ብፁዕ ነው፥ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ቢያቈስልም ይጠግናልና፥ ቢሰብርም፥ እጆቹ ይፈውሳሉና። ከስድስት ችግሮች ያድንሃል፥ በሰባተኛውም ውስጥ ክፋት አትነካህም። በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ጊዜ ከሰይፍ እጅ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፥ የጥፋት አደጋ ሲመጣም አትፈራም። በጥፋት አደጋና በራብ ላይ ትስቃለህ፥ የምድረ በዳ አራዊትንም አትፈራም፥ ቃል ኪዳንህ ከምድረበዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፥ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና። ድንኳንህ ሰላምን እንደሚያገኝም ታውቃለህ፥ በረትህን ትጐበኛለህ፥ አንዳችም አይጐድልብህም። ዘርህም እንደሚበዛ፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር ብዙ እንደሚሆን ታውቃለህ። የእህሉ ነዶ ወራቱ ሲደርስ ወደ አውድማ እንደሚገባ፥ ዕድሜ ጠግበህ ወደ መቃብር ትገባለህ። እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፥ አንተም ለራስህ እወቀው።”
መጽሐፈ ኢዮብ 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 5:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች