መጽሐፈ ኢዮብ 33

33
1“እንግዲህ፥ ኢዮብ ሆይ፥ ንግግሬን እንድትሰማ፥
ቃሌንም ሁሉ እንድታደምጥ እለምንሃለሁ።
2እነሆ፥ ለመናገር ተዘጋጅቻለሁ፥
አንደበቴም ቃላትን አሰናድቷል።
3ቃሎቼ የልቤን ቅንነት ያሳያሉ፥
ከንፈሮቼም የሚያውቁትን በቅንነት ይናገራሉ።
4የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥
ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ።
5ይቻልህ እንደሆነ መልስልኝ፥
የምትለውን አዘጋጅተህ በፊቴ ቁም።
6እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ፥
እኔም እንዳንተ ከጭቃ የተቀረጽሁ ነኝ።
7እነሆ፥ ግርማዬ አያስፈራህም፥
እኔም አልጫንህም።”
8“በጆሮዬ ተናግረሃል፥
የቃልህንም ድምፅ ሰምቻለሁ፤ እንዲህም ብለሃል፦
9‘እኔ ንጹሕ ነኝ፥ በደል የለብኝም፤
ያለ እንከን ነኝ፥ ኃጢአትም የለብኝም፥
10እነሆ፥ ሊወቅሰኝ ምክንያት ይፈጥራል፥
እንደ ጠላቱም ይቈጥረኛል፥
11 # ኢዮብ 13፥27። እግሬን በግንዶች መካከል ያጣብቃል፥
መንገዶቼን ሁሉ ይቆጣጠራል።’
12እነሆ፥ አንተ በዚህ አቋምህ ትክክል አይደለህም፥
‘እግዚአብሔር ከሰው ይበልጣል’ ብዬ እመልስልሃለሁ።
13አንተ፦ ‘በፍጹም ለቃሌ መልስ አይሰጥም’ ብለህ፥
ስለምን ከእርሱ ጋር ትከራከራለህ?
14እግዚአብሔር በአንድም በሁለትም መንገድ ይናገራል፥
ሰው ግን አያስተውለውም።
15 # ኢዮብ 4፥13። በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥
አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥
በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥
16በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥
በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥
17ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ፥
ሰውንም ከትዕቢት ይቆጥበው ዘንድ፥
18ነፍሱን ከጉድጓድ፥
በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል።”
19“ደግሞ በአልጋ ላይ በስቃይ ይገሥጸዋል፥
አጥንቱም ሁሉ ያለማቋረጥ ይንቀጠቀጣል።
20ሕይወቱም እንጀራን፥
ነፍሱም ጣፋጭ መብልን ትጠላለች።
21ሥጋው እስከማይታይ ድረስ ይሰለስላል፥
ተሸፍኖ የነበረውም አጥንት ይገለጣል።
22ነፍሱ ወደ ጉድጓዱ፥
ሕይወቱም ወደሚገድሉአት ቀርባለች።
23የቀናውን መንገድ ለሰው ያስታውቀው ዘንድ፥
ከሺህ አንድ ሆኖ የሚተረጉም መልአክ ቢገኝለት፥
24እየራራለት፦
እሱን መታደጊያ ቤዛ አግኝቻለሁና
ወደ መቃብር እንዳይወርድ አድነው ቢለው፥
25ሥጋው እንደ ልጅ ሥጋ ይለመልማል፥
ወደ ወጣትነቱም ጊዜ ይመለሳል።
26ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥
እርሱም ይሰማዋል፥
ፊቱንም በደስታ ያሳየዋል፥
ለሰውም የጽድቁን ዋጋ ይመልስለታል።
27እርሱም በሰው ፊት እየዘመረ፦
እኔ በድያለሁ፥ ቀናውንም አጣምሜአለሁ፥
የሚገባኝንም ቅጣት አልተቀበልሁም፥
28ነፍሴ ወደ መቃብር እንዳትወርድ አድኖአታል፥
ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች ይላል።”
29“እግዚአብሔር ይህን ሁሉ
ሁለት ጊዜና ሦስት ጊዜ ከሰው ጋር ያደርጋል፥
30ይህም ነፍሱን ከመቃብር ይመልስ ዘንድ፥
በሕያዋንም ብርሃን ያበራ ዘንድ ነው።
31ኢዮብ ሆይ፥ አድምጥ፥ እኔንም ስማ፥
ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ።
32የምትናገረው ቢኖርህ መልስልኝ፥
ትክክል መሆንህን እወድዳለሁና ተናገር።
33አለበለዚያም እኔን ስማ፥
ዝም በል፥ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ