መጽሐፈ ኢዮብ 32
32
1ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ሰዎች መመለስን ተዉ። 2ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቁጣ ነደደ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው። 3እንዲሁም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ። 4ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ኤሊሁ ከኢዮብ ጋር የሚናገርበትን ጊዜ ይጠባበቅ ነበር። 5ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አንደበት መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቁጣው ነደደ።
6የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦
“እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፥
ስለዚህም ሰጋሁ፥ የማውቀውን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ።
7እንደዚህም አልሁ፦ ‘ዕድሜ ይናገር፥
ረጅም ዕድሜም ጥበብን ያስታውቅ።’
8ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥
ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል።
9በዕድሜ ያረጁ የግድ ጠቢባን አይደሉም፥
ሽማግሌዎችም የግድ ፍርድን አያስተውሉም።
10ስለዚህም፦ ‘ስሙኝ፥
እኔ ደግሞ እውቀቴን ልግለጥላችሁ’ አልሁ።”
11“እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥
የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ
ሙግታችሁን አዳመጥሁ።
12እንዲሁም ልብ በማድረግ ሰማኋችሁ፥
እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥
ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም።
13እናንተም፦ ጥበብን አግኝተናል፥
እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ።
14እርሱ እኔን አይደለም የተናገረው፥
እኔም በእናንተ አነጋገር ዓይነት አልመልስለትም።
15እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም፥
የሚናገሩትንም አጡ።
16እነርሱ አልተናገሩምና፥
ቆመው ዳግመኛ አልመለሱምና እኔ በትዕግሥት እጠብቃለሁን?
17እኔ ደግሞ ፈንታዬን እመልሳለሁ፥
እውቀቴንም እገልጣለሁ፥
18እኔ በቃላት ተሞልቻለሁና፥
በውስጤም ያለ መንፈስ አስገድዶኛልና።
19እነሆ፥ አንጀቴ በአዲስ ወይን ጠጅ ተሞልቶ ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥
መውጫም እንደሚፈልግ ወይን ጠጅ ሆነ።
20ጥቂት እንድተነፍስ እናገራለሁ፥
ከንፈሮቼን ከፍቼ እመልሳለሁ።
21በማንም ሰው ፊት ግን አላደላም፥
ማንንም አላቈላምጥም።
22በማቈላመጥ መናገር አላውቅምና፥
ያለዚያስ ፈጣሪዬ ፈጥኖ ባጠፋኝ ነበር።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 32: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ