መጽሐፈ ኢዮብ 15
15
1ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“በውኑ ጠቢብ ሰው እንደ ነፋስ በሆነ እውቀት ይመልሳልን?
ሆዱንስ በምሥራቅ ነፋስ ይሞላልን?
3ከማይረባ ነገር፥
ወይስ ከማይጠቅም ንግግር ጋር ይዋቀሳልን?
4አንተም ፈሪሃ እግዚአብሔርን እስከ መተው ደርሰሃል፥
በእግዚአብሔርም ፊት አምልኮን ታስቀራለህ።
5በደልህ ንግግርህን ይመራዋል፥
የተንኰለኞችንም አንደበት ትመርጣለህ።
6የሚፈርድብህ አፍህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፥
ከንፈሮችህም ይመሰክሩብሃል።”
7“በውኑ መጀመሪያ የተወለደው የሰው ልጅ አንተ ነህን?
ከተራሮች በፊትስ ተፀንሰሀልን?
8የእግዚአብሔርንስ ምሥጢር ሰምተሃልን?
ጥበብን የግልህ ለማድረግ ትመኛለህን?
9እኛ ሳናውቀው አንተ የምታወቀው ምንድነው?
ከእኛ ዘንድስ ሳይኖር የምታስተውለው ምንድነው?
10በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ
ሽበትም ያላቸው ሽማግሌዎችም ከእኛ ጋር አሉ።
11በውኑ የእግዚአብሔር ማጽናናት፥
በየውሃትም የተነገረህ ቃል ጥቂት ነውን?
12ልብህስ ለምን ወደ ሌላ ይወስድሃል?
ዐይኖችህስ ለምን ይገላምጣሉ?
13ቁጣህን በእግዚአብሔር ላይ እስከ ማንሣት ደርሰህ፥
እነኚህንም ቃላት ከአፍህ እስከ ማውጣት ደርሰህ።
14 #
ኢዮብ 25፥4-6። ከንጹሕ ለመመደብ የሰው ልጅ ምንድነው?
ጻድቅስ ለመባል ከሴት የተወለደ ምንድነው?
15እነሆ፥ ቅዱሳኑን#15፥15 መላእክቱን። እንኳን አያምናቸውም፥
ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።
16ታዲያ አስጸያፊና የረከሰ፥
በደልን እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?!”
17“ስማኝ ልንገርህ፥ እነሆም ያየሁትን ልተርክልህ፤
18ጠቢባን የተናገሩትን፥ አባቶቻቸውም ያልሰወሩትን፤
19ምድሪቱ ለእነርሱ ብቻ ተሰጥታለችና፥ በመካከላቸውም እንግዳ አልገባባቸውም።
20ክፉ ሰው ዕድሜ ልኩን ሲሠቃይ ይኖራል፥
እንዲሁም ግፈኛ በተመደቡለት ዓመታት በሙሉ።
21የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ነው፥
በሰላምም ሳለ ቀማኛ ይመጣበታል።
22ከጨለማ ተመልሼ እወጣለሁ ብሎ አያምንም፥
ሰይፍም ይሸመቅበታል።
23ተቅበዝብዞም፦ ወዴት አለ? እያለ እንጀራ ይለምናል፥
የጨለማ ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል።
24መከራና ጭንቀት ያስፈራሩታል፥
ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ንጉሥ ያሸንፉታል።
25እጁን በእግዚአብሔር ላይ ዘርግቶአልና፥
ሁሉን የሚችል አምላክን ደፍሮአልና፥
26በደንዳና አንገቱና በወፍራሙ ጋሻው
እየገሠገሠ ወደ እርሱ ይመጣበታልና፥
27በስብም ፊቱን ከድኖአልና፥
በውፍረትም ወገቡ ተሸፍኗልና፥
28በተደመሰሱም ከተሞች ውስጥ፥
ሰውም በሌለባቸው፥
ክምር ለመሆን በተመደቡ ቤቶች ውስጥ ተቀምጦአልና
29ባለ ጠጋ አይሆንም፥ ሀብቱም አይጸናም፥
ጥላውንም በምድር ላይ አይጥልም፥
30ከጨለማ አይወጣም፥
ነበልባሉም ቅርንጫፎቹን ያደርቃቸዋል፥
አበባዎቹም ይረግፋሉ።
31ራሱን እያሳተ በከንቱ ነገር አይታመን
ዋጋው ከንቱ ነገር ይሆናልና።
32ቀኑ ሳይደርስ ጊዜው ይፈጸማል፥
ቅርንጫፉም አይለመልምም።
33እንደ ወይን ያልበሰለውን ዘለላ ያረግፋል፥
እንደ ወይራ አበባውን ይጥላል።
34የአምላክ አልባ ሰው ጉባኤ ፍሬ የለውም፥
የጉቦ ድንኳኖችንም እሳት ትበላለች።
35ጉዳትን ይፀንሳሉ፥ በደልንም ይወልዳሉ፥
ሆዳቸውም ተንኰልን ያዘጋጃል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 15: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ