ትንቢተ ኤርምያስ 44

44
ጣዖትን ማውገዝ
1በግብጽ ምድር በሚግዶልና በጣፍናስ በሜምፎስም በጳትሮስም አገር ስለ ተቀመጡ አይሁድ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ያመጣሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ራሳችሁ አይታችኋል፤ እነሆ፥ ዛሬ ባድማ ሆነዋል፥ የሚቀመጥባቸውም የለም። 3ይህም የሆነው ስለ ሠሩት ክፋት እኔን ስላስቈጡኝ፥ በዚህም እናንተም አባቶቻችሁም እነርሱም ለማያውቁአቸው ለሌሎች አማልክት ለማጠንና ለማገልገል ስለ ሄዱ ነው። 4ሆኖም በማለዳ ተነሥቼ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ እንዲህ ብዬ ላክሁባችሁ፦ ‘እባካችሁ፥ እንደዚህ ያለ የጠላሁትን ርኩስ ነገር አታድርጉ።’ 5ነገር ግን አልሰሙም ከክፋታቸውም ተመልሰው ለሌሎች አማልክት ላለማጠን ጆሮአቸውን አላዘነበሉም። 6ስለዚህ መዓቴና ቁጣዬ ወረዱ፥ በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ነደዱ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ፈረሱ ባድማም ሆኑ። 7አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከይሁዳ ወገን መካከል ትሩፍ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ልጅንና ሕፃንን ከእናንተ ለማጥፋት ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? 8እናንተም እንድትጠፉ በምድርም አሕዛብ ሁሉ መካከል መረገሚያና መሰደቢያ እንድትሆኑ፥ ለመቀመጥ በገባችሁባት በግብጽ ምድር ለሌሎች አማልክት አጥናችሁ በእጃችሁ ሥራ ለምን ታስቈጡኛላችሁ? 9በውኑ በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያደረጉትን የአባቶቻችሁን ክፋት፥ የይሁዳንም ነገሥታት ክፋት፥ የሚስቶቻቸውንም ክፋት፥ የእናንተንም ክፋት፥ የሚስቶቻችሁንም ክፋት ረስታችሁታልን? 10እስከ ዛሬ ድረስ አልተዋረዱም አልፈሩምም፥ በእናንተና በአባቶቻችሁም ፊት ባኖርሁት ሕጌና ሥርዓቴ አልሄዱም።
11“ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይሁዳን ሁሉ ለማጥፋት ፊቴን ለክፋት በእናንተ ላይ አደርጋለሁ። 12ወደ ግብጽም ለመግባት በዚያም ለመቀመጥ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ትሩፍ እወስዳለሁ፥ ሁሉም ይጠፋሉ፥ በግብጽም ምድር ይወድቃሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለመሣቀቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ። 13ኢየሩሳሌምን በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እንደ ቀጣሁ፥ እንዲሁ በግብጽ ምድር የሚኖሩትን እቀጣለሁ። 14ስለዚህም በግብጽ ምድር በዚያ ለመቀመጥ ከገቡት ከይሁዳ ትሩፍ ማናቸውም ተመልሰው ለመቀመጠጥ ወደ ሚመኙበት ወደ ይሁዳ ምድር አያመልጡም በሕይወትም አይተርፉም አይመለሱምም፤ ከአንዳንድ ከሚያመልጡ በቀር አይመለሱም።”
15ሚስቶቻቸውም ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ሰዎች ሁሉ በዚያም ቆመው የነበሩ ሴቶች ሁሉ፥ በግብጽ ምድር በጳትሮስ የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ መለሱለት እንዲህም አሉ፦ 16“አንተ በጌታ ስም የነገርኸንን ቃል አንሰማህም። 17ነገር ግን እኛና አባቶቻችን ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ እንዳደረግነው፥ ለሰማይ ንግሥት ለማጠን የመጠጥንም ቁርባን ለእርሷ ለማፍሰስ ከአፋችን የወጣውን ቃል ሁሉ በእርግጥ እናደርጋለን፤ በዚያን ጊዜም እንጀራ እንጠግብ ነበር፥ መልካምም ይሆንልን ክፉም አናይም ነበር። 18ለሰማይ ንግሥት ማጠንን ለእርሷም የመጠጥን ቁርባን ማፍሰስን ከተውን ወዲህ ግን፥ እኛ ሁሉ ነገር ጐድሎብናል፥ በሰይፍና በራብ አልቀናል። 19እኛስ ለሰማይ ንግሥት ባጠንንላት የመጠጥንም ቁርባን ባፈሰስንላት ጊዜ፥ በውኑ ያለ ባሎቻችን ፈቃድ ምስልዋ ያለበት እንጐቻ አድርገንላታልን? የመጠጥንስ ቁርባን አፍስሰንላታልን?”
20ኤርምያስም ይህን ቃል ለመለሱለት ሕዝብ ሁሉ፥ ለወንዶቹና ለሴቶቹ ለሕዝቡም ሁሉ፥ መለሰላቸው እንዲህም አለ፦ 21“እናንተና አባቶቻችሁ ነገሥታቶቻችሁም አለቆቻችሁም የምድሪቱም ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያጠናችሁትን ዕጣን ጌታ አያስታውሰውምን? በልቡስ አያኖረውምን? 22ጌታም ከእንግዲህ ወዲህ የሥራችሁን ክፋትና ያደረጋችሁትን ርኩሰት መታገሥ አልቻለም፤ ስለዚህ ምድራችሁ ባድማ መሣቀቂያም መረገሚያም ሆናለች ዛሬም እንደሆነ የሚኖርባት የለም። 23ስላጠናችሁ፥ በጌታም ላይ ኃጢአትን ስለ ሠራችሁ፥ የጌታንም ድምፅ ስላልሰማችሁ፥ በሕጉና በሥርዓቱም በምስክሩም ስላልሄዳችሁ፥ ስለዚህ ዛሬ እንደሆነ ይህ ክፉ ነገር ደርሶባችኋል።”
24ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ለሴቶቹም ሁሉ እንዲህ አለ፦ “በግብጽ ምድር የምትገኙ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ስሙ። 25የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናንተና ሚስቶቻችሁ በአፋችሁ፦ ‘ለሰማይ ንግሥት ለማጠን የመጠጥንም ቁርባን ለእርሷ ለማፍሰስ የተሳልነውን ስእለታችንን በእርግጥ እንፈጽማለን’ ብላችሁ ተናገራችሁ በእጃችሁም አደረጋችሁት፤ እንግዲህ ስእለታችሁን አጽኑ ስእለታችሁንም ፈጽሙ። 26ስለዚህ እናንተ በግብጽ ምድር የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ስሙ፤ በግብጽ ምድር ሁሉ በሚኖር በይሁዳ ሰው ሁሉ አፍ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ፦ ‘ሕያው በሆነ ጌታ እግዚአብሔር እምላለሁ!’ ተብሎ እንዳይጠራ፥ እነሆ፥ በታላቅ ስሜ ምያለሁ፥ ይላል ጌታ። 27እነሆ፥ ለመልካም ሳይሆን ለክፋት በእነርሱ ላይ እመለከታለሁ፤ በግብጽም ምድር ያሉት የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ያልቃሉ። 28ከሰይፍም ያመለጡት ጥቂት ሰዎች ከግብጽ ምድር ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሳሉ፤ በዚያም ለመቀመጥ ወደ ግብጽ ምድር የገቡት የይሁዳ ትሩፍ ሁሉ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማናችን ቃል እንደሚጸና በውኑ ያውቃሉ! 29ቃሎቼም በእናንተ ላይ ለክፋት በእርግጥ እንደሚጸኑ እንድታውቁ በዚህች ስፍራ እቀጣችኋለሁ፤ ይህም ለእናንተ ምልክት ይሆናል፥ ይላል ጌታ። 30#2ነገ. 25፥1-7።ጌታ እንዲህ ይላል፦ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ጠላቱ ለሆነው ነፍሱንም ለሚሻው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፥ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የግብጹን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራን ለጠላቶቹ ነፍሱንም ለሚሽዋት እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ