የጭፍራ አለቆችም ሁሉ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የሆሻያም ልጅ ያእዛንያ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ቀረቡ፥ ነቢዩንም ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “በዐይኖችህ እንደምታየን ከብዙ ጥቂት ተርፈናልና ልመናችን እባክህ፥ በፊትህ ትድረስ፥ ስለ እኛና ስለዚህ ትሩፍ ሁሉ ለጌታ ለአምላክህ ጸልይ፥ ጌታ አምላክህም የምንሄድበትን መንገድና ማድረግ የሚገባንን ነገር ያሳውቀን ይሆናል።” ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰምቻችኋለሁ፤ እነሆ፥ እንደ ቃላችሁ ወደ ጌታ ወደ አምላካችሁ እጸልያለሁ፤ ጌታም የሚመልስላችሁን ቃል ሁሉ እነግራችኋለሁ፥ ከእናንተም ምንም አልሸሽግም።” እነርሱም ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “ጌታ አምላክህ በአንተ አማካይነት ወደ እኛ የላከውን ቃል ሁሉ ባናደርግ፥ ጌታ በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁንብን። የአምላካችንን የጌታን ድምፅ በመስማታችን መልካም እንዲሆንልን፥ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ እኛ ወደ እርሱ የምንልክህን የአምላካችንን የጌታን ድምፅ እንሰማለን።” ከዐሥር ቀን በኋላ የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። ኤርምያስም የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆች ሁሉ፥ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ፥ እንዲህም አላቸው፦ ጸሎታችሁን በፊቱ እንዳቀርብ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስላደረግሁባችሁ ክፉ ነገር ተጸጽቻለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ አንጻችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም። የምትፈሩትን የባቢሎንን ንጉሥ አትፍሩት፤ እናንተን ለማዳን ከእጁም ለመታደግ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና እርሱን አትፍሩ፥ ይላል ጌታ። እርሱ እንዲምራችሁ ወደ አገራችሁም እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ።
ትንቢተ ኤርምያስ 42 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 42:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች