ትንቢተ ኤርምያስ 42

42
ነቢዩ ኤርምያስ የተማረኩት እንዳይመለሱ መምከሩ
1የጭፍራ አለቆችም ሁሉ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የሆሻያም ልጅ ያእዛንያ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ቀረቡ፥ 2ነቢዩንም ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “በዐይኖችህ እንደምታየን ከብዙ ጥቂት ተርፈናልና ልመናችን እባክህ፥ በፊትህ ትድረስ፥ ስለ እኛና ስለዚህ ትሩፍ ሁሉ ለጌታ ለአምላክህ ጸልይ፥ 3ጌታ አምላክህም የምንሄድበትን መንገድና ማድረግ የሚገባንን ነገር ያሳውቀን ይሆናል።” 4ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰምቻችኋለሁ፤ እነሆ፥ እንደ ቃላችሁ ወደ ጌታ ወደ አምላካችሁ እጸልያለሁ፤ ጌታም የሚመልስላችሁን ቃል ሁሉ እነግራችኋለሁ፥ ከእናንተም ምንም አልሸሽግም።” 5እነርሱም ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “ጌታ አምላክህ በአንተ አማካይነት ወደ እኛ የላከውን ቃል ሁሉ ባናደርግ፥ ጌታ በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁንብን። 6የአምላካችንን የጌታን ድምፅ በመስማታችን መልካም እንዲሆንልን፥ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ እኛ ወደ እርሱ የምንልክህን የአምላካችንን የጌታን ድምፅ እንሰማለን።”
7ከዐሥር ቀን በኋላ የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። 8ኤርምያስም የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆች ሁሉ፥ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ፥ 9እንዲህም አላቸው፦ ጸሎታችሁን በፊቱ እንዳቀርብ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ 10ስላደረግሁባችሁ ክፉ ነገር ተጸጽቻለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ አንጻችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም። 11የምትፈሩትን የባቢሎንን ንጉሥ አትፍሩት፤ እናንተን ለማዳን ከእጁም ለመታደግ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና እርሱን አትፍሩ፥ ይላል ጌታ። 12እርሱ እንዲምራችሁ ወደ አገራችሁም እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ። 13እናንተ ግን፦ በዚህች ምድር አንቀመጥም ብትሉ የአምላካችሁንም የጌታን ድምፅ ባትሰሙ፥ 14እናንተም፦ አይደለም፤ ጦርነት ወደማናይባት የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማባት ወደማንራብባትም ወደ ግብጽ ምድር እንሄዳለን በዚያም እንቀመጣለን ብትሉ፥ 15እናንተ የይሁዳ ትሩፍ ሆይ! እንግዲህ አሁን የጌታን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ግብጽ ለመግባት በዚያም ሄዳችሁ ለመቀመጥ በእርግጥ ፊታችሁን ብታቀኑ፥ 16የምትፈሩት ሰይፍ በዚያ በግብጽ ምድር ይደርስባችኋል፥ የሚያስደነግጣችሁም ራብ በዚያ በግብጽ ይከተላችኋል፥ በዚያም ትሞታላችሁ። 17ወደ ግብጽም ለመግባት በዚያም ለመቀመጥ ፊታቸውን ያቀኑ ሰዎች ሁሉ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታሉ፤ እኔም ከማመጣባቸው ክፉ ነገር ከእነርሱ አንድም ሰው በሕይወት አይተርፍም፥ አንድም ሰው አያመልጥም።
18የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ተናግሮአልና፦ ቁጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ወረደ፥ እንዲሁ ወደ ግብጽ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይወርድባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለመሣቀቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ትሆናላችሁ፥ ይህንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩትም። 19እናንተ የይሁዳ ትሩፍ ሆይ! ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአችኋል፦ ወደ ግብጽ አትግቡ፤ ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ እወቁ፤ 20እናንተ፦ ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ ጌታ ጸልይ፥ ጌታ አምላካችንም የሚናገረውን ሁሉ ንገረን እኛም እናደርገዋለን ብላችሁ ወደ ጌታ ወደ አምላካችሁ እናንተው ልካችሁኝ ነበርና ራሳችሁን አታልላችኋል። 21እኔም ዛሬ ነገርኋችሁ፥ እናንተ ግን ወደ እናንተ በላከኝ ነገር ሁሉ የአምላካችሁን የጌታን ድምፅ አልሰማችሁም። 22ስለዚህም አሁን ሄዳችሁ ለመቀመጥ በወደዳችሁበት በዚያ ስፍራ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እንደምትሞቱ በእርግጥ እወቁ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ