መጽሐፈ ዮዲት 11
11
ዮዲት ከሆሎፎርኒስ ጋር ያደረገችው
የመጀመሪያው ትውውቅ
1ሆሎፎርኒስም እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት አይዞሽ፥ ልብሽም አይፍራ፥ የምድር ሁሉ ገዢ የሆነውን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ለማገልገል የቆረጠን ሰው ጉዳት አድርሼ አላውቅምና። 2አሁንም ቢሆን በተራራማው አገር የሚኖሩ ወገኖችሽ ባይንቁኝ ኖሮ በእርሱ ላይ ጦሬን ባላነሣሁም ነበር፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በራሳቸው ላይ አመጡ። 3እስቲ አሁን ንገሪኝ፥ ከእነርሱ ሸሽተሽ ወደ እኛ ለምን መጣሽ? ሆኖም ወደ መዳን መጥተሻል፥ አይዞሽ፥ ዛሬና ለሁልጊዜም ትኖሪአለሽ። 4ማንም ጉዳት አያደርስብሽም፤ እንዲያውም ለጌታዬ ለንጉሥ ናቡከደነፆር ባርያዎች እንደሚደረግላቸው ለአንቺም መልካም ይደረግልሻል።” 5ዩዲትም እንዲህ አለችው፦ “የባርያህን ቃል ተቀበል፤ ባርያህ በፊትህ ትናገር፤ በዚች ምሽት ለጌታዬ አንድም የሐሰት ነገርን አልናገርም። 6የባርያህን ቃል ከተከተልህ፥ እግዚአብሔር በአንተ ሥራህን ሁሉ ከፍፃሜ ያደርሰዋል፤ ጌታዬም ዕቅዱን ከማሳካት አይወድቅም። 7#ኤር. 34፥6፤ ዳን. 2፥38።የምድር ሁሉ ንጉሥ፥ ሕያው ፍጥረትን ሁሉ እንድታቀና በላከህ ናቡከደነፆርና በኃይሉ እምላለሁ፤ በአንተ በኩል ሰዎች ብቻ የሚገዙለት አይደሉም፤ ነገር ግን የዱር አራዊትና ከብቶች፥ በሰማይ የሚበሩ ወፎችም በኃይልህ ከናቡከደነፆርና ከቤቱ በታች ይገዙለታል እንጂ።”
8“ጥበብህንና ክህሎትህን ሰምተናል፥ በመንግሥቱ ሁሉ አንተ ብቻ መልካም፥ በአስተዋይነትህ ኃያል፥ በሰልፍህም ሁሉ የተደነቅህ እንደሆንህ በምድሪቱ ሁሉ ተሰምቷል። 9አኪዮርም በጉባኤህ ላይ ያደረገውን ንግግር ሰምተናል፤ ሕይወቱን ላተረፉት የቤቱሊያ ሰዎችም ለአንተ የነገረህን ሁሉ ነግሮአቸዋል። 10ስለዚህ ጌታዬ ሆይ እርሱ የተናረገውን አቅልለህ አትመለከተው። ነገር ግን እውነት ስለሆነ በልብህ አኑረው፤ ሕዝባችን አይቀጣም፤ እግዚአብሔርን ካልበደሉ በስተቀር ሰይፍም ሊያጠፋቸው አይችልም። 11አሁን ግን ጌታዬ የተጣለና የማይረባ እንዳይሆን ሞት በፊታቸው ይወድቅባቸዋል፤ ኃጢአት በእነርሱ ላይ ይዟቸዋል፥ የአምላካቸውን ቁጣ አስነስተዋል፥ ይህም ከመንገዳቸው ስለወጡ ነው። 12የምግባቸው ስላለቀና ውኃው ስላጠራቸው፥ ከብቶቻቸውን ሁሉና እግዚአብሔር በሕጉ እንዳይበሉ የከለከላቸውን ሁሉ ሊበሉ ወስነዋል። 13#ዘፀ. 23፥19፤ ዘሌ. 27፥30።በኢየሩሳሌም በአምላካችን ፊት ለሚያገለግሉ ካህናት የተለየውን፥ ከሕዝቡ አንድም ሰው በእጁ ሊነካቸው የማይፈቀድለትን የእህሉን በኵራትና የወይኑንና የዘይቱን አስራት ሊበሉ ወስነዋል። 14ከሽማግሌዎች ጉባኤ ፈቃድ እንዲያመጡላቸው ወደ ኢየሩሳሌም ላኩ፤ በዚያ የሚኖሩ ሰዎች እንዲህ አድርገዋልና። 15መልሱ ሲደርሳቸውና የወሰኑትንም በፈጸሙ ሰዓት፥ በዚያች ቀን እንዲጠፉ በእጅህ ይሰጣሉ። 16ስለዚህ እኔ ባርያህ ይህን በአወቅሁ ጊዜ ከፊታቸው ኰበለልሁ፤ በምድር ሁሉ ያለ፥ የሰማውን ሁሉ ስለ እነርሱ በሰማ ጊዜ የሚደነቅበት ሥራ ከአንተ ጋር እንድሠራ እግዚአብሔር ላከኝ። 17ባርያህ የሰማይን አምላክ ቀንና ሌሊት የምታገለግል፥ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ናት፤ ስለዚህ ጌታዬ ከአንተ ጋር እቆያለሁ፤ ነገር ግን ባርያህ በየምሽቱ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ ወደ ሸለቆው ትወርዳለች፤ እርሱም ኃጢአትን በሰሩ ጊዜ ይነግረኛል። 18በዚያን ጊዜ መጥቼ እነግርሃለሁ፥ አንተም ከሠራዊትህ ሁሉ ጋር ትወጣለህ፥ ከእነርሱም የሚቋቋምህ አይኖርም። 19ወደ ኢየሩሳሌም እስክትደርስ ድረስ በይሁዳ መካከል እመራሃለሁ፤ በዚያም ዙፋንህን እዘረጋልሃለሁ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጐች ትመራቸዋለህ፥ ውሻም ምላሱን በአንተ ላይ አያንቀሳቅስም፤ ይህ አስቀድሞ ተነግሮኛል፤ ይህም ተብራራልኝ፥ ለአንተም እንድነግርህ ተላክሁ።” 20ንግግርዋ ሆሎፎርኒስንና አገልጋዮቹን ደስ አሰኛቸው። በጥበቧ ተደነቁ፥ እንዲህም አሉ፦ 21“ከምድር ጫፍ እስከ ጫፍ በፊት ውበትና በአነጋገር ጥበብ እንደዚህች ሴት ያለ የለም።” 22ሆሎፎርኒስም እንዲህ አለ፦ “ኃይል በእጃችን፥ ጥፋት ግን ጌታዬን በካዱት ላይ እንዲሆን ከሕዝቡ ቀድሞ የላከሽ እግዚአብሔር መልካም አደረገ። 23አሁንም አንቺ ውብ እና አንደበተ ርቱዕ ነሽ፤ እንደተናገርሽው ከአደረግሽ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል፥ አንቺም በንጉሥ ናቡከደነፆር ቤት ትኖሪያለሽ፤ ስምሽም በምድር ሁሉ ይታወቃል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዮዲት 11: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ