ትንቢተ ኢሳይያስ 58:3-7

ትንቢተ ኢሳይያስ 58:3-7 መቅካእኤ

“ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም?” ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ለማሰማት ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነው? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነው? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ እንዲያደርግ፥ ማቅንና አመድንም በበታቹ እንዲያነጥፍ ነው? በውኑ ይህን ጾም፥ በጌታ ዘንድ የተወደደ ቀን ብለህ ትጠራዋለህ? እኔስ የመረጥሁት ጾም፥ የበደልን እስራት እንድትፈቱ፥ የቀንበርንስ ጠፍር እንድትለቁ፥ የተገፉትን አርነት እንድታወጡ፥ ቀንበሩን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ እንድትቈርስ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ እንድታስገባ፥ የተራቈተውን ብታይ እንድታለብሰው፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?