እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። እንጀራ ላልሆነ ነገር ገንዘብን ለምን ታባክናላችሁ፥ የድካማችሁንም ዋጋ በማያጠግብ ነገር ለምን ትለውጣላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ሰውነታችሁ በሕይወት እንድትኖር ስሙኝ፥ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘለዓለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ። እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ ጌታ የማያውቅህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣል። ጌታ በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ ጌታም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፤ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል ጌታ። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ እንድታበቅልና እንድታፈራም እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ፥ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃል እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል፤ የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልል ይላሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። በእሾህም ፈንታ ጥድ፥ በኩርንችትም ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ ለጌታም መታሰቢያና ለዘለዓለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።
ትንቢተ ኢሳይያስ 55 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 55:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች