ወደ ዕብራውያን 12:1-12

ወደ ዕብራውያን 12:1-12 መቅካእኤ

እንግዲህ እነደዚህ ዓይነት ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ማንኛውንም ሸክምና የተጣበቅንበትን ኅጢአት ሁሉ አራግፈን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። የእምነታችንንም ራስና ፍጽምና የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፥ ውርደቱንም ንቆ፥ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ እንዴት እንደተቋቋመ አስቡ። ከኃጢአት ጋር በምታደርጉት ተጋድሎ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤ እንደ ልጆችም እንዲህ በማለት የተነገራችሁን ምክር ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ! የጌታን ተግሣጽ አታቅልል፤ በሚገሥጽህም ጊዜ ተስፋ አትቁረጥ፤ ጌታ የሚወደውን ይገሥጻልና፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ሁሉ ይቀጣል።” እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፥ የተግሣጽን ቅጣት ታገሡ፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ሁሉም ተካፋይ ከሆኑበት ቅጣት ውጭ ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በተጨማሪ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር፤ ታዲያ እንዴት በላቀ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር አይገባንም? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበር፤ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ለጊዜው ቅጣት ሁሉ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰላማዊ የጽድቅን ፍሬ ያፈራላቸዋል። ስለዚህ የላሉትን እጆቻችሁን የሰለሉትንም ጉልበቶቻችሁን አቅኑ።