ኦሪት ዘፍጥረት 7:5-18

ኦሪት ዘፍጥረት 7:5-18 መቅካእኤ

ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ። የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በመጣ ጊዜ የኖኅ ዕድሜ ስድስት መቶ ዓመት ነበረ። ኖኅ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ሚስቶቻቸው ከጥፋት ውሃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገቡ። ከንጹሕ እንስሳ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰውም ሁሉ፥ ጥንድ ተባዕትና እንስት እየሆኑ፥ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ ኖኅ ወደ መርከቡ ገቡ። ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ መጣ። ኖኅ ስድስት መቶ ዓመት በሆነው፥ በሁለተኛው ወር፥ ከወሩም በዓሥራ ሰባተኛው ቀን ላይ፥ ከምድር በታች ያለው የታላቁ ጥልቅ መፍለቂያዎች ሁሉ በድንገት ተነደሉ፥ የሰማያትም መስኮቶች ተከፈቱ፥ ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዘነበ። በዚያውም ቀን ኖኅ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም፥ ካም፥ ያፌትና የኖኅ ሚስት፥ ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ወደ መርከብ ገቡ። ከእነርሱ ጋር፥ ከአራዊት፥ ከእንስሶች፥ በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና በሰማይ ከሚበርሩ ወፎች ከእያንዳንዱ ዓይነት አብረዋቸው ገቡ። በዚህ ዓይነት እስትንፋስ ካላቸው ፍጥረቶች ከእያንዳንዱ ዓይነት ሁለት ሁለት እየሆኑ ከኖኅ ጋር ወደ መርከቡ ገቡ፤ ፍጥረት ሁሉ ወንድና ሴት ሆነው ወደ መርከቡ የገቡት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ፤ ጌታም በስተ ኋላው ዘጋበት። የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን አላቋረጠም፥ ውኃውም በዛ፥ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም በላይ ከፍ አለች። ውሃ በምድር ላይ እያደገና እየበረታ በሄደ መጠን መርከቡ በውሃው ላይ መንሳፈፍ ጀመረ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}