ኦሪት ዘፍጥረት 14:12-24
ኦሪት ዘፍጥረት 14:12-24 መቅካእኤ
በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ። አንድ የሸሸ ሰውም መጣ፥ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፥ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የባሉጥ ዛፎች አጠገብ ይኖር ነበር፥ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ። አብራምም ጠላቶቹን ለማጥቃት አገልጋዮቹን በቡድን ከፋፍሎ በሌሊት እርሱ ከባርያዎቹ ጋር ወረደባቸው፥ መታቸውም፥ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ። ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰ በኋላም የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፥ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። እንዲህም ሲል ባረከውም፦ አብራም ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፥ ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ፥ ልዑል እግዚአብሔርም ይባረክ፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው። የሰዶም ንጉሥም አብራምን፦ ሰዎቹን ስጠኝ፥ ከብቱን ግን ለአንተ ውሰድ አለው። አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፦ ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፥ አንተ፦ አብራምን ባለ ጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ፥ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ።

