ዘፍጥረት 14:12-24
ዘፍጥረት 14:12-24 NASV
የአብራም ወንድም ልጅ ሎጥ፣ ሰዶም ይኖር ስለ ነበር እርሱንም ማርከው ንብረቱንም ዘርፈው ሄዱ። ከዚህም ያመለጠ አንድ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ይህን ነገረ፤ አብራም በዚያ ጊዜ ይኖር የነበረው በአሞራዊው መምሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ ነበር። መምሬ፣ ወንድሞቹ ኤስኮልና አውናን የአብራም የኪዳን አጋሮቹ ነበሩ። አብራም የወንድሙን ልጅ መማረክ እንደ ሰማ በቤቱ ተወልደው አድገው የሠለጠኑ 318 ጦረኞች አሰልፎ እስከ ዳን ድረስ ገሠገሠ። አብራም ጠላቶቹን ለማጥቃት ሰራዊቱን ሌሊቱን በቡድን በቡድን ከፋፍሎ ከደማስቆ በስተሰሜን እስከሚገኘው እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። አብራም ጠላት የማረከውን በሙሉ አስጣለ፤ የወንድሙን ልጅ ሎጥን፣ ንብረቱን እንዲሁም ሴቶቹንና ሌሎቹን ምርኮኞች አስመለሰ። አብራም ኮሎዶጎምርንና ዐብረውት የተሰለፉትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፣ የሰዶም ንጉሥ፣ “የንጉሥ ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የልዑል አምላክ ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ አብራምንም እንዲህ ሲል ባረከው፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል አምላክ አብራምን ይባርክ፤ ጠላቶችህን አሳልፎ በእጅህ የሰጠህ፣ ልዑል አምላክ ይባረክ።” አብራምም ከሁሉ ነገር ዐሥራትን አውጥቶ ሰጠው። የሰዶም ንጉሥም አብራምን፣ “ሰዎቹን ለእኔ ስጠኝ፤ ንብረቱን ግን ለራስህ አስቀር” አለው። አብራም ግን ለሰዶም ንጉሥ እንዲህ አለው፤ “ሰማይንና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር፣ ወደ ልዑል አምላክ እጆቼን አንሥቻለሁ፤ ‘አብራምን አበለጸግሁት’ እንዳትል፣ ብጣሽ ክርም ሆነ የጫማ ማሰሪያ እንኳ ከአንተ አንዳች አልፈልግም። ሰዎቼ ከበሉትና ከእኔ ጋራ ከሄዱት ሰዎች ድርሻ በቀር ለራሴ አንዳች ነገር አልቀበልም፤ አውናን፣ ኤስኮልና መምሬ ድርሻቸውን ይውሰዱ።”

