ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1:12-23

ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1:12-23 መቅካእኤ

በብርሃን የቅዱሳንን ርስት እንድንካፈል ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑት ነው። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ልጁ መንግሥት አፈለሰን፤ በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአትን ስርየት አገኘን። እርሱም ለማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው፤ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በእርሱ አብሮ ተዋቅሮአል። እርሱም አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር ቀዳሚ በመሆን መጀመሪያ ነው፤ ከሙታንም በኩር ነው። እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ በማደሩ ተደስቷል፤ በመስቀሉም ደም ሰላምን በማድረግ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእርሱ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታርቋል። እናንተም ከእርሱ ተለይታችሁና ክፉ በመሥራት በሐሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በእርሱ ፊት ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ቅዱሳን አድርጎ ለማቅረብ በሥጋዊው አካሉ በሞቱ አስታረቃችሁ። ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት የምትጸኑ ከሆነ ነው፤ ይህም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፤ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ።

ከ ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1:12-23ጋር የተዛመዱ ነፃ የንባብ እቅዶች እና ምንባቦች