2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:1-11

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:1-11 መቅካእኤ

ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ከተቀመጠና ጌታም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፥ ነቢዩን ናታንን፥ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው። ናታንም፥ “ጌታ ካንተ ጋር ስለሆነ፥ በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ” አለው። በዚያች ሌሊት ግን የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፤ “ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን፥ ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤተ መቅደስ የምትሠራልኝ አንተ ነህን?’ እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም ከእስራኤላውያን ሕዝብ ጋር በተጓዝሁበት ስፍራ ሁሉ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው መሪዎቻቸው አንዱን፥ ‘ከዝግባ ዕንጨት ለምን ቤት አልሠራህልኝም?’ ያልሁት አለን? አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤ በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አስወገድሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ የራሱ የሆነ መኖሪያ እንዲኖረውና ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይናወጥ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጠዋለሁ፤ አጸናዋለሁም። ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቁነውም፤ ከዚህ በፊት እንደ ሆነው፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ እንዳደረጉበት ከእንግዲህ አያደርጉበትም፤ ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ። ከዚህም በላይ ጌታ ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤