2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 25
25
የኢየሩሳሌም በጠላት እጅ መውደቅ
(2ዜ.መ. 36፥13-21፤ ኤር. 52፥3-11)
1 #
ኤር. 21፥1-10፤ 34፥1-5፤ ሕዝ. 24፥2። ከዚህ በኋላ ናቡከደነፆር መላው ሠራዊቱን አስከትቶ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፥ ዐሥረኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ወታደሮቹ ከከተማይቱ ውጪ ሰፍረው ዙሪያውን የሚከብብ የዐፈር ቁልል ሠሩ፤ 2ከበባውም እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛ ዓመት ዘመነ መንግሥት ድረስ ቆየ፤ 3በዚያው ዓመት አራተኛው ወር በገባ በዘጠነኛው ቀን ራቡ በጣም ስለ ጸና ሕዝቡ የሚመገበው አንዳችም ምግብ አልነበረም። 4#ሕዝ. 33፥21።የከተማይቱ ቅጽሮች ተጣሱ፤ የባቢሎን ወታደሮች ከተማይቱን ዙሪያውን ከበው በመያዝ ቢጠብቁም እንኳ የይሁዳ ንጉሥ ወታደሮች በሌሊት አምልጠው ወጡ፤ ወደ ንጉሡ የአትክልት ቦታ ከሚያስገባው መንገድ ተነሥተው ሁለቱን ቅጽሮች በሚያያይዘው የቅጽር በር በኩል በማለፍ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ አቅጣጫ ሸሹ። 5የባቢሎን ሠራዊት ግን ንጉሥ ሴዴቅያስን እያሳደደ በኢያሪኮ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ ማረከው፤ ወታደሮቹም ጥለውት ሸሹ፤ 6ሴዴቅያስም ተይዞ በሪብላ ከተማ ወደሚገኘው ወደ ናቡከደነፆር ተወሰደ፤ በዚያም ናቡከደነፆር ፍርድ አስተላለፈበት፤ 7#ሕዝ. 12፥13።ይኸውም ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየ ልጆቹ በፊቱ ታረዱ፤ ከዚህም በኋላ ናቡከደነፆር የሴዴቅያስን ዐይኖች አውጥቶ አሳወረው፤ እጆቹንም በሰንሰለት አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው።
የቤተ መቅደሱ መፍረስ
(ኤር. 52፥12-33)
8ናቡከደነፆር በባቢሎን በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት፥ አምስተኛው ወር በገባ በሰባተኛው ቀን ናቡዛርዳን ተብሎ የሚጠራው የናቡከደነፆር የክብሩ ዘበኞቹ አዛዥ ኢየሩሳሌም ገባ። 9#1ነገ. 9፥8።እርሱም ቤተ መቅደሱን፥ ቤተ መንግሥቱን፥ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የታላላቅ ሰዎችን ቤቶችና በከተማው ውስጥ የሚገኙትንም ሌሎች ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ 10በክብር ዘቡ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ወታደሮች የኢየሩሳሌም ዙሪያ አጥር 11ከዚህም በኋላ ናቡዛርዳን በከተማይቱ ቀርተው የነበሩትንና ሌሎችን ሰዎች፥ እንዲሁም ከድተው ወደ ባቢሎናውያን የተጠጉትን ሁሉ ይዞ ወደ ባቢሎን አጋዛቸው፤ 12ነገር ግን ምንም ሀብት የሌላቸውን የመጨረሻ ድኾች፥ አትክልት ኰትኳቾችና መሬት አራሾች ይሆኑ ዘንድ በይሁዳ ምድር ትቶአቸው ሄደ።
13 #
1ነገ. 7፥15-26፤ 2ዜ.መ. 3፥15-17፤ 1ነገ. 7፥23-26፤ 2ዜ.መ. 4፥2-5። ባቢሎናውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን የነሐስ ዐምዶች፥ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችና ከነሐስ የተሠራውን ታላቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ሰባበሩ፤ ነሐሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 14#1ነገ. 7፥45፤ 2ዜ.መ. 4፥16።እነርሱም ምንቸቶችን፥ መጫሪያዎችን፥ መኰስተሪያዎችን፥ የዕጣን ማስቀመጫዎችንና ከነሐስ የተሠሩ የቤተ መቅደሱ መገልገያ ዕቃዎችን ሁሉ ወሰዱ። 15ጽናዎችንና ዱካዎችን ከብርና ከወርቅ የተሠሩ በመሆናቸው ወሰዱአቸው። 16ንጉሥ ሰሎሞን ለቤተ መቅደስ ያሠራቸውን ሁለቱን ዐምዶች፥ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችና ታላቁን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ፥ በክብደታቸው ምክንያት ሊመዝኑአቸው አልቻሉም። 17አንዱ ዐምድ ስምንት ሜትር ነበረው፤ ጉልላቱ ከነሐስ የተሠራ ነበር፤ የጉልላቱም ቁመት አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በዙሪያውም ከነሐስ በተሠራ መረብ ላይ የሮማን ፍሬ ቅርጽ የመሰለ ፈርጠኛ ጌጥ ተሠርቶበት ነበር።
የይሁዳ ነዋሪዎች ተማርከው ወደ ባቢሎን መወሰዳቸው
(ኤር. 52፥24-27)
18የሠራዊቱ አዛዥ ናቡዛርዳን ሊቀ ካህናቱን ሤራያን በማዕረግ የእርሱ ምክትል የሆነውን ካህኑን ሶፎንያስና ሦስቱን የቤተ መቅደስ ዘበኞች እስረኛ አድርጎ ወሰዳቸው፤ 19ከከተማይቱም የወታደሮች አዛዥ የሆነው አንድ ባለ ሥልጣን፥ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በከተማይቱ የነበሩትን አምስቱን የንጉሥ አማካሪዎች፥ የአገሩን ሕዝብ ለወታደርነት ይመለምል የነበረውን መኰንንና ሌሎችንም ሥልሳ ሰዎችን ወሰደ፤ 20ናቡዛርዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ በሐማት ግዛት በምትገኘው በሪብላ ከተማ ወደነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወሰዳቸው፤ 21ንጉሡም በዚያ እነርሱን አስደብድቦ በማሠቃየት በሞት ቀጣቸው።
በዚህም ዓይነት የይሁዳ ሕዝብ ከአገራቸው ተማርከው ተወሰዱ።
ገዳልያ የይሁዳ ገዢ መሆኑ
(ኤር. 40፥7-9፤ 41፥1-3)
22 #
ኤር. 40፥7-9። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የሳፋን የልጅ ልጅ የአሒቃም ልጅ ገዳልያን ወደ ባቢሎን ተማርከው ሳይወሰዱ ለቀሩት ሰዎች ሁሉ ኃላፊ ይሆን ዘንድ የይሁዳ ገዢ አድርጎ ሾመው። 23እጃቸውን ያልሰጡ የይሁዳ የጦር መኰንኖችና ወታደሮች የባቢሎን ንጉሥ ገዳልያን ገዢ አድርጎ እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ ወደ ምጽጳ መጥተው ከእርሱ ጋር ተገናኙ፤ እነዚህም የጦር መኰንኖች የነታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬሐ ልጅ ዮሐናን፥ የነጦፋ ከተማ ተወላጅ የሆነው የታንሑሜት ልጅ ሠራያና የማዕካ ተወላጅ የሆነው የዛንያ ነበሩ፤ 24ገዳልያም እነርሱንና ወታደሮቻቸውን እንዲህ አላቸው፤ “ከባቢሎናውያን ባለ ሥልጣኖች የተነሣ ምንም ዓይነት ፍርሀት ሊያድርባችሁ እንደማይገባ ቃል እገባላችኋለሁ፤ በዚህች ምድር ኑሮአችሁን መሥርቱ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ገብሩ፤ ይህን ብታደርጉ ሁሉ ነገር ይቃናላችኋል።”
25 #
ኤር. 41፥1-3። ነገር ግን በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ንጉሣዊ ዘር የነበረውና የኤሊሻማዕ የልጅ ልጅ የሆነው የነታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ምጽጳ ሄደ፤ በዚያም አደጋ ጥሎ ገዳልያን ገደለው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተገኙትን እስራኤላውያንንና ባቢሎናውያንን ሁሉ ገደለ፤ 26#ኤር. 43፥5-7።ከዚህም የተነሣ ባቢሎናውያንን ስለ ፈሩ እስራኤላውያን ሀብታሞችም ድኾችም ከጦር ሠራዊት መኰንኖች ጋር በአንድነት ተነሥተው ወደ ግብጽ ሸሹ።
ኢኮንያን ከእስራት መፈታቱ
(ኤር. 52፥31-34)
27ዮርማሮዴቅ ኤዊልመሮዳክ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ከእስራት በመፍታት ምሕረት አደረገለት፤ ይህም የሆነው ኢኮንያን በእስረኛነት ተማርኮ በሄደ በሠላሳ ሰባት ዓመቱ በዐሥራ ሁለተኛው ወር በሃያ ሰባተኛው ቀን ነው። 28ኤዊልመሮዳክ ለዮአኪን መልካም ነገር አደረገለት፤ እንደ እርሱ ተማርከው በባቢሎን በስደት ከሚኖሩ ነገሥታት ሁሉ የላቀ የክብር ማዕርግ ሰጠው፤ 29ስለዚህም ኢኮንያን በእስር ቤት የነበረውን ልብስ ለውጦ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማእድ እንዲመገብ ተፈቀደለት፤ 30በኖረበት ዘመን ሁሉ በየቀኑ ለማናቸውም ለሚያስፈልገው ነገር ያውለው ዘንድ የዘወትር ቀለብ ይሰጠው ነበር።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 25: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ