2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 24

24
1 # ኤር. 25፥1-38፤ ዳን. 1፥1፤2። ኢዮአቄም በነገሠ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይሁዳን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ከገበረለት በኋላ እንደገና ዐመፀ፤ 2እግዚአብሔር ባገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት ይሁዳን ስለ ማጥፋት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ወራሪ ቡድኖች ባቢሎናውያንን፥ ሶርያውያንን፥ ሞአባውያንንና ዐሞናውያንን በኢዮአቄም ላይ አስነሣበት። 3ይህም ሁሉ የሆነው ንጉሥ ምናሴ ስለ ፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የይሁዳን ሕዝብ ከፊቱ ለማስወገድ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ነው፤ 4በተለይም ምናሴ የንጹሓን ሰዎችን ደም በማፍሰሱና ኢየሩሳሌምንም በንጹሓን ደም በመሙላቱ ምክንያት ይህ ሁሉ ሊፈጸም ችሎአል፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ለምናሴ ምሕረት ሊያደርግለት አልፈቀደም።
5ኢዮአቄም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 6ኢዮአቄም ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢኮንያን ነገሠ።
7የባቢሎን ንጉሥ ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ግብጽ ሰሜናዊ ጠረፍ ድረስ የግብጽ ይዞታ የነበረውን ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ስለ ነበረ የግብጽ ንጉሥና ሠራዊቱ ከዚያን በኋላ ከግብጽ ውጪ ዘመቻ አላደረጉም፤
የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን
(2ዜ.መ. 36፥9-10)
8ኢኮንያን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ገዛ፤ እናቱም ነሑሽታ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ የሆነው የኤልናታን ልጅ ነበረች። 9አባቱ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
10በናቡከደነፆር የጦር አዛዦች የሚመራው የባቢሎን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ዘምቶ የከበባትም በዚሁ በዮአኪን ዘመነ መንግሥት ነበር። 11በከበባውም ጊዜ ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ 12#ኤር. 22፥24-30፤ 24፥1-10፤ 29፥1፤2።ንጉሥ ኢኮንያን ከእናቱ፥ ከልዑላን መሳፍንቱ፥ ከጦር አዛዦቹና ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለ ሥልጣኖች ጋር ቀርቦ ለባቢሎናውያን እጁን ሰጠ፤ ናቡከደነፆር በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ኢኮንያንን እስረኛ አድርጎ ያዘው፤ 13በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ ጠራርጎ ወደ ባቢሎን ወሰደ። ቀደም ሲል እግዚአብሔር በተናገረውም ቃል መሠረት ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አሠርቶት የነበረውን የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰባበረው። 14ናቡከደነፆር የኢየሩሳሌምን ሕዝብ፥ ልዑላን መሳፍንቱን ሁሉና ሌሎችንም ታላላቅ ሰዎችን ጭምር በድምሩ ዐሥር ሺህ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፤ ከእነርሱም ጋር የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎችንና የብረት አንጣሪዎችን ሁሉ ወሰደ፤ በይሁዳ እንዲቀሩ ያደረገው የመጨረሻዎችን ድኾች ብቻ ነበር።
15 # ሕዝ. 17፥12። ናቡከደነፆር ኢኮንያንን አስሮ ከነእናቱ ከሚስቶቹ፥ ባለሟሎቹ ከሆኑ ባለሥልጣኖችና ከይሁዳ ታላላቅ ሰዎች ጋር በአንድነት ሰብስቦ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። 16የባቢሎን ንጉሥ ሰባት ሺህ ለውጊያ ብቃት ያላቸው ወንዶችን፥ እንዲሁም አንድ ሺህ ብረት ቀጥቃጮችንና እደ ጥበበኞችን ወደ ባቢሎን ወሰደ።
17 # ኤር. 37፥1፤ ሕዝ. 17፥13። ናቡከደነፆር በኢኮንያን ምትክ ማታንያ ተብሎ የሚጠራውን የዮአኪንን አጐት በይሁዳ አነገሠ፤ ስሙንም በመለወጥ ሴዴቅያስ ብሎ ጠራው።
የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ
(2ዜ.መ. 36፥11-12ኤር. 52፥1-3)
18 # ኤር. 27፥1-22፤ 28፥1-17። ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሀያ አንድ ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሐሙጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የነበረው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፤ 19ኢዮአቄም ባደረገው ዓይነት ሴዴቅያስ ክፉ አደረገ። 20#ሕዝ. 17፥15።እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሕዝብ ላይ ተቆጥቶ ከፊቱ አስወገዳቸው፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ