የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን፥ ኩታ፥ ዓዋ፥ ሐማትና ሰፋርዋይም ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ። እነርሱም በዚያ ሰፍረው መኖር እንደ ጀመሩ እግዚአብሔርን አላመለኩትም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር አንበሶችን በመላክ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ሰባብረው እንዲገድሉ አደረገ፤ ለአሦርም ንጉሠ ነገሥት “በሰማርያ ከተሞች ሰፍረው እንዲኖሩ ያደረግሃቸው ሕዝቦች የዚያችን አገር አምላክ ሕግ የሚያውቁ ሆነው አልተገኙም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰባብሮ የሚገድሉ አንበሶችን ላከባቸው” የሚል ወሬ ደረሰው። ስለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ “ማርከን ካመጣናቸው ካህናት አንዱን ወደዚያ ላኩ፤ ወደዚያም ተመልሶ በመሄድ የዚያችን አገር አምላክ ያዘዘውን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምራቸው አድርጉ” ሲል አዘዘ። ስለዚህም ከሰማርያ ተማርኮ የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ካህን ተመልሶ በመሄድ በቤትኤል ተቀመጠ፤ በዚያም ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባው አስተማረው። በሰማርያ የሰፈሩት ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን ጣዖት መሥራት ቀጥለው እስራኤላውያን ባሠሩአቸው በከፍተኛ ማምለኪያ ቦታዎች አኖሩአቸው፤ እያንዳንዱ ቡድን በሚኖርበት ከተማ ሁሉ የየራሱን ጣዖት አቆመ። በዚህም ዓይነት የባቢሎን ሰዎች ሱኮትበኖት በተባለው አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ እንዲሁም የኩታ ሰዎች ኔርጋል ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፥ ጣዖት ሠሩ፤ የሐማት ሕዝብ ኢሺማ ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፤ ጣዖት ሠሩ፤ የዓዋ ሕዝብ ኒብሐዝና ታርታቅ ተብለው በሚጠሩ አማልክታቸው ስም ጣዖቶቻቸውን ሠሩ፤ የሰፋርዋይምም ሕዝብ አድራሜሌክና ዓናሜሌክ ተብለው ለሚጠሩ አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እነዚሁ ሰዎች በተጨማሪ ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ነበር። ከእያንዳንዳቸውም ቡድን በአረማውያን የማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸውን ካህናት መረጡ፤ በዚህም ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ይኖሩባቸው በነበሩት ሕዝቦች ይፈጽሙት በነበረው ልማድ መሠረት ለባዕዳን አማልክታቸው ይሰግዱ ነበር። ይህንኑ አሮጌ ልማዳቸውን እስከ አሁን ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን አያመልኩም፤ ወይም ስሙ እስራኤል ተብሎ ለተጠራው ለያዕቆብ ልጆች እግዚአብሔር በሰጣቸው ደንቦች፥ ሥርዓቶች፥ ሕጎችና ትእዛዞች ጸንተው አልኖሩም። እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ፤ ለእነርሱም አገልጋዮች በመሆን አትስገዱላቸው፤ መሥዋዕትንም አታቅርቡላቸው፤ በታላቅ ኃይልና በሥልጣን ከግብጽ ምድር ላወጣኋችሁ ለእኔ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ መስገድና መሥዋዕት ማቅረብ የሚገባችሁ ለእኔ ብቻ ነው፤ ጽፌ የሰጠኋችሁንም ድንጋጌና ሥርዓቱን፥ ሕጎችና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ጠብቁ፤ ባዕዳን አማልክትንም አትከተሉ፤ እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ባዕዳን አማልክትንም አታምልኩ፤ እኔን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እኔም ከጠላቶቻችሁ እጅ በመታደግ አድናችኋለሁ።” ነገር ግን እነዚያ አሕዛብ ይህን መስማት ትተው አሮጌ ልማዳቸውን ተከተሉ። እነዚያ ሕዝቦች በዚሁ ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ለጣዖቶቻቸው ይሰግዱ ነበር፤ ዘሮቻቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ዓይነት አምልኮ እንደ ቀጠሉ ናቸው።
2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 17 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 17:24-41
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች