2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 34:8-28

2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 34:8-28 መቅካእኤ

በነገሠም በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የጌታን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የጌታን የአምላኩን ቤት እንዲጠግኑ ላካቸው። ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም የደጆቹም ጠባቂዎች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ ጌታ ቤት ያመጡትን ገንዘብ ሰጡት። የጌታንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ በጌታም ቤት የሚሠሩት ሠራተኞች ቤቱን ለሚጠግኑና ለሚያድሱ ሠራተኞች ሰጡ። እነርሱም የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች እንዲሠሩ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ እንዲገዙ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ። ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹም የደጁም ጠባቂዎች ከሌዋውያን ወገን ነበሩ። ወደ ጌታም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የጌታን የሕግ መጽሐፍ አገኘ። ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን፦ “የሕጉን መጽሐፍ በጌታ ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም እንዲህ ብሎ አወራለት፦ “ባርያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ እያደረጉ ነው፤ በጌታም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፥ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ።” ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ፦ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። ንጉሡም የሕጉን ቃላት በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለማድረግ አባቶቻችን የጌታን ቃል ስላልጠበቁ፥ በእኛ ላይ የነደደው የጌታ ቁጣ እጅግ ታላቅ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት ጌታን ጠይቁ።” ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ የላካቸው ሰዎች ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርሷም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንንም ነገር ነገሩአት። እርሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ አመጣለሁ። በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቁጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። ጌታን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃላት፥ ልብህ ተጸጽቶአልና፥ በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ የተናገርሁትን ቃላቴን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፥ ይላል ጌታ። እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩባትም ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።