ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፣ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን፣ የከተማዪቱን ገዥ መዕሤያንና የጸሓፊውን የኢዮአካዝን ልጅ ኢዮአክን የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይጠግኑ ዘንድ ላካቸው። እነርሱም ወደ ሊቀ ካህኑ ወደ ኬልቅያስ ሄደው፣ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጣውን ገንዘብ ሰጡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች የነበሩት ሌዋውያን፣ ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና ከመላው የእስራኤል ቅሬታዎች እንደዚሁም ከመላው ይሁዳና ከብንያም፣ ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር። እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ዐደራ ሰጡ፤ እነዚህም ሰዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን ለጠገኑትና ላደሱት ሰዎች ከፈሉ። እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈርሱ ላደረጓቸው ሕንጻዎች ጥርብ ድንጋዮችን፣ ሠረገላዎችንና ማገጣጠሚያ ዕንጨቶችን እንዲገዙ ለየእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ለግንበኞች ገንዘብ ሰጡ። ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ። የበላይ ሆነው አመራር የሚሰጧቸውም ከሜራሪ ጐሣ የሆኑት ሌዋውያን፣ ኢኤትና አብድዩ፣ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። በዜማ ዕቃ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ሌዋውያን ሁሉ፣ የጕልበት ሠራተኞች ኀላፊ በመሆን፣ በየሥራው ላይ የተመደቡትን ሠራተኞች ይቈጣጠሩ ነበር። ጥቂቶቹ ሌዋውያን ደግሞ ኀላፊዎች፣ ጸሓፊዎችና በር ጠባቂዎች ነበሩ። ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ፣ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” አለው፤ ከዚያም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፤ “ሹማምትህ የታዘዙትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።” ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት። ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ከዚያም ንጉሡ ኬልቅያስን፣ የሳፋን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ ዓብዶንን፣ ጸሓፊውን ሳፋንንና የንጉሡን የቅርብ አገልጋይ ዓሳያን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ሄዳችሁ ስለ እኔ እንደዚሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስላሉት ትሩፋን በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ። አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ በላያችን ላይ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ቍጣ ታላቅ ነውና፤ በዚህ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት አልተመላለሱምና።” ኬልቅያስና ንጉሡ ከርሱ ጋራ የላካቸው ሰዎች የአልባሳት ጠባቂ የነበረው የሐስራ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የሴሌም ሚስት ወደሆነችው ወደ ነቢዪቱ ወደ ሕልዳና ሄደው ነገሯት። እርሷም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው የከተማው ክፍል ትኖር ነበር። ነቢዪቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ በተጻፈው ርግማን ሁሉ መሠረት፣ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎቹ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ። እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና በእጆቻቸው ሥራ ሁሉ ለቍጣ ስላነሣሡኝ፣ ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገረውን በሰማህ ጊዜ፣ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔር ፊት ራስህን ስላዋረድህ፣ ራስህን ዝቅ አድርገህ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ ስላለቀስህ፣ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ፤ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታ እና በነዋሪዎቹ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ሰዎቹም መልሷን ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።
2 ዜና መዋዕል 34 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ዜና መዋዕል 34
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ዜና መዋዕል 34:8-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች